የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9:3-13

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 9:3-13 አማ05

ንጉሡም “እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ቸርነት የማሳየው ከሳኦል ቤተሰብ ከሞት የተረፈ ሰው አለን?” ሲል ጺባን ጠየቀው። ጺባም “ከዮናታን ወንዶች ልጆች አንዱ አሁንም በሕይወት አለ፤ እርሱም እግረ ሽባ ነው” ሲል መለሰ። ንጉሡም “የት ነው ያለው?” ሲል ጠየቀ። ጺባም “በሎደባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ሲል መለሰ። ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት መፊቦሼትን ከሎደባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው። የሳኦል የልጅ ልጅ፥ የዮናታን ልጅ መፊቦሼት በመጣ ጊዜ በዳዊት ፊት ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት አክብሮቱን ገለጠ። ዳዊትም “መፊቦሼት!” ሲል ጠራው። መፊቦሼትም “ጌታ ሆይ! እነሆ አገልጋይህ ነኝ!” ሲል መለሰ። ዳዊትም “አይዞህ አትፍራ! ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል ቸርነት አደርግልሃለሁ፤ የአያትህ የሳኦል ይዞታ የነበረውን መሬት ሁሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም በማእዴ ተቀምጠህ ትመገባለህ” አለው። መፊቦሼትም በአክብሮት እጅ ነሥቶ “የሞተ ውሻ ልመመስል ለእኔ ለአገልጋይህ ይህን ያኽል ቸርነት የምታደርግልኝ ለምንድን ነው?” ከዚህ በኋላ ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ጺባን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የሳኦልና የቤተሰቡ ንብረት የነበረውን ማናቸውንም ነገር የጌታህ የልጅ ልጅ ለሆነው ለመፊቦሼት እሰጣለሁ፤ አንተ፥ ወንዶች ልጆችህና አገልጋዮችህ ለጌታህ ለሳኦል ቤተሰብ ምድሪቱን አርሳችሁ ምግብ ይሆናቸው ዘንድ መከሩን አገቡላቸው፤ የጌታህ የልጅ ልጅ መፊቦሼት ግን ዘወትር በገበታዬ የሚቀርብ ተመጋቢ ይሆናል፤” ጺባ ዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆችና ኻያ አገልጋዮች ነበሩት። ጺባም “ንጉሥ ሆይ! እኔ አገልጋይህ አንተ ያዘዝከውን ሁሉ እፈጽማለሁ” ሲል መለሰ። በዚህ ዐይነት መፊቦሼት ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ተቈጥሮ በንጉሥ ገበታ እየቀረበ ይመገብ ነበር። መፊቦሼት ሚካ የተባለ ወጣት ልጅ ነበረው፤ የጺባ ቤተሰብ አባሎች በሙሉ የመፊቦሼት አገልጋዮች ሆኑ፤ ስለዚህ ሁለቱም እግሮቹ ሽባ የሆኑት መፊቦሼት በንጉሡ ገበታ እየቀረበ በመመገብ የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሆነ።