የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ሳሙኤል 9:3-13

2 ሳሙኤል 9:3-13 NASV

ንጉሡም፣ “የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዳደርግለት ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው የለምን?” ሲል ጠየቀው። ሲባም ለንጉሡ፣ “እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፣ “የት ነው ያለው?” ብሎ ጠየቀ። ሲባም፣ “ሎደባር በተባለ ስፍራ በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት ይገኛል” ብሎ መለሰለት። ስለዚህም ንጉሥ ዳዊት፣ ሜምፊቦስቴን ከዓሚኤል ከማኪር ቤት ከሎደባር ልኮ አስመጣው። የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት በመጣ ጊዜ፣ አክብሮቱን ለመግለጥ ለጥ ብሎ እጅ ነሣ። ዳዊትም፣ “ሜምፊቦስቴ” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “እነሆ፤ አገልጋይህ” አለ። ዳዊትም፣ “አትፍራ፤ ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ስል በርግጥ ቸርነት አደርግልሃለሁና። የአባትህን የሳኦልን ምድር በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ ዘወትርም ከማዕዴ ትበላለህ” አለው። ሜምፊቦስቴ ለጥ ብሎ እጅ ነሣና፣ “እንደ ሞተ ውሻ ለምቈጠር ለእኔ ይህን ያህል የምታደርግልኝ አገልጋይህ ኧረ ማን ነኝ?” አለ። ከዚያም ንጉሡ የሳኦልን አገልጋይ ሲባን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “የሳኦልና የቤተ ሰቡ የሆነውን ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቼዋለሁ። አንተ፣ ልጆችህና አገልጋዮችህ የጌታችሁ የልጅ ልጅ የሚበላውን እንዲያገኝ መሬቱን ዕረሱለት፣ ምርቱንም አግቡለት። የጌታህ የልጅ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ምን ጊዜም ከማእዴ ይበላል።” በዚያ ጊዜ ሲባ ዐሥራ ዐምስት ወንዶች ልጆችና ሃያ አገልጋዮች ነበሩት። ከዚያም ሲባ ንጉሡን፣ “ጌታዬ ንጉሥ፣ አገልጋዩን ያዘዘውን ሁሉ፣ አገልጋይህም ይፈጽመዋል” አለው። ስለዚህም ሜምፊቦስቴ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ሆኖ ከዳዊት ማእድ ይበላ ነበር። ሜምፊቦስቴ ሚካ የተባለ አንድ ትንሽ ልጅ ነበረው፤ የሲባ ቤተ ሰዎች በሙሉ ሜምፊቦስቴን ያገለግሉት ነበር። ሜምፊቦስቴም ሁልጊዜ ከንጉሥ ማእድ ስለሚበላ ይኖር የነበረው በኢየሩሳሌም ነው፤ ሁለት እግሮቹም ሽባ ነበሩ።