ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5:11-25

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5:11-25 አማ05

የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ይሠሩለት ዘንድ አናጢዎች፥ ግንበኞችና የሊባኖስ ዛፍ እንጨት አስይዞ መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ። ዳዊትም እግዚአብሔር የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና ለሕዝቡም ሲል መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገለት ተገነዘበ። ዳዊት ከኬብሮን ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሚስቶችና ቁባቶች እንዲኖሩት አደረገ። ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወልደውለት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም የተወለዱት ልጆች፥ ሻሙዓ፥ ሾባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ይብሐር፥ ኤሊሹዓ፥ ኔፌግ፥ ያፊዓ፥ ኤሊሻማዕ፥ ኤልያዳዕና ኤሊፌሌጥ ነበሩ። ዳዊት በእስራኤል ላይ መንገሡን ፍልስጥኤማውያን ሰሙ፤ ስለዚህም ሠራዊታቸው ዳዊትን ለመማረክ ገሥግሦ ሄደ፤ ዳዊት የእነርሱን መምጣት በሰማ ጊዜ ወደ ተመሸገ ስፍራ ወረደ፤ ፍልስጥኤማውያንም በራፋይም ሸለቆ ሰፍረው ለዝርፊያ ተበታትነው ተሰማሩ። ዳዊትም “በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ልጣልባቸውን? ድልንስ ትሰጠኛለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አዎ በእነርሱ ላይ አደጋ ጣልባቸው! እኔ በእነርሱ ላይ ድልን እሰጥሃለሁ!” ሲል መለሰለት። ስለዚህም ዳዊት ወደ ባዓል ፈራጺም ወርዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል ካደረገ በኋላ “እግዚአብሔር በጠላቶቼ መካከል እንደ ጐርፍ ሰባብሮ ገባ” አለ፤ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም “ባዓል ፈራጺም” ተብሎ ተጠራ። ፍልስጥኤማውያን በሸሹ ጊዜ ጣዖቶቻቸውን ጥለው ሄዱ፤ ዳዊትና ተከታዮቹም ማርከው ወሰዱአቸው። ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን ወደ ራፋይም ተመልሰው እንደገና ሰፍረው ለዝርፊያ ተሰማሩ። ዳዊትም እንደገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰለት “አሁን ካለህበት በኩል በእነርሱ ላይ አደጋ አትጣል፤ ነገር ግን ከወዲያ በኩል በስተ ኋላ በመዞር ከሾላ ዛፎች ፊት ለፊት ሆነህ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ። በሾላ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ለመምታት የወጣ መሆኑን ዐውቀህ ፈጥነህ አጥቃ።” ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም አሸነፈ፤ ከጌባዕ አንሥቶ እስከ ጌዜር ድረስም አባረራቸው።