2 ሳሙኤል 5:11-25

2 ሳሙኤል 5:11-25 NASV

በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ድንጋይ ጠራቢዎችን ዐብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት። ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም ሲል መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት ተገነዘበ። ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤ ቁባቶችንም አስቀመጠ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት። በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ያፍያ፣ ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ። ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ፍለጋ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊትም ይህን ሰምቶ ወደ ምሽጉ ወረደ። በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። ስለዚህም ዳዊት፣ “በፍልስጥኤማውያን ላይ ወጥቼ ልምታቸውን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ሂድ፤ በርግጥ ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው። ስለዚህም ዳዊት ወደ በኣልፐራሲም ሄዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው። እርሱም “የጐርፍ ውሃ ጥሶ በመውጣት እንደሚያፈራርስ፣ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በፊቴ አፈራረሳቸው” አለ። ከዚህ የተነሣም የዚያ ቦታ ስም “በኣልፐራሲም” ተባለ። ፍልስጥኤማውያንም ጣዖቶቻቸውን ትተው ሸሽተው ስለ ነበር፣ ዳዊትና ሰዎቹ ወስደው አቃጠሏቸው። ፍልስጥኤማውያን እንደ ገና መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበታትነው ሰፈሩ። ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በስተ ኋላቸው በኩል በመክበብ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ በቀጥታ ወዳሉበት አትውጣ፤ በሾላ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ጕዞ ድምፅ ስትሰማም፣ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት ቀድሞህ ወጥቷል ማለት ነውና በዚያ ጊዜ በፍጥነት ወደ ፊት ሂድ።” ስለዚህም ዳዊት እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ከገባዖን እስከ ጌዝር ድረስ እያሳደደ መታቸው።