ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22:1-18

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22:1-18 አማ05

እግዚአብሔር ዳዊትን ከሳኦልና ከሌሎቹም ጠላቶቹ እጅ በመታደግ ባዳነው ጊዜ ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ክብር ዘመረ፦ እግዚአብሔር አለቴ፥ አምባዬ የደኅንነቴ ኀይል፥ ጠንካራ ምሽጌ ነው። አንተ የመዳን አለቴ ነህ፤ እንዲሁም ጋሻዬ፥ የጦር መሣሪያዬና ከለላዬ ነህ፤ ከኀያላን እጅ ታድነኛለህ። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ እርሱም ከጠላቶቼ ያድነኛል። የሞት ጣር ከበበኝ፤ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ፤ የሲኦል ገመድ ተበተበኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ፤ መከራ በደረሰብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም አምላኬን ለመንኩት። በመቅደሱም ሆኖ ድምፄን ሰማ ጩኸቴንም አደመጠ። እግዚአብሔር ስለ ተቈጣ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤ የአድማስ መሠረቶች ተናጉ፤ ተነቃነቁም። ከአፍንጫው የቊጣ ጢስ ወጣ፤ ከአፉም የሚባላ የእሳት ነበልባልና የሚያቃጥል ፍም ወጣ። ሰማይን ሰንጥቆ ወደ ታች ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቊር ደመና ነበረ፤ በኪሩቤል ላይ ሆኖ በረረ፤ በነፋስም ክንፎች ላይ ሆኖ መጠቀ። ሁለንተናውን በጨለማ ሸፈነ። በውሃ የተሞላ ጥቅጥቅ ያለ ደመና ከቦታል። በፊቱ ካለው ነጸብራቅ የተነሣ ጥቅጥቅ ያለ ደመና፥ በረዶና የሚነድ እሳት መጣ። እግዚአብሔር ከሰማይ አንጐዳጐደ፤ ልዑል እግዚአብሔር ድምፁን አሰማ። ፍላጻውን ከቀስቱ አስፈነጠረ፤ ጠላቶቹንም በተናቸው፤ በመብረቁም ብልጭታ አሳደዳቸው። እግዚአብሔርም ከአፍንጫው ከሚወጣው የእስትንፋስ ወላፈንና በግሣጼው የባሕሩ ውስጥ ወለል ታየ፥ የምድሩም መሠረት ተገለጠ። እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ እጁን በመዘርጋት ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሃም ስቦ አወጣኝ። በጣም በርትተውብኝ ከነበሩት ከኀይለኞች ጠላቶቼና ከሚጠሉኝ ሰዎች ሁሉ እጅ እግዚአብሔር አዳነኝ።