የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19

19
የኢዮአብ ዳዊትን መውቀሱ
1ንጉሥ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም ሞት በብርቱ አዝኖ በማልቀስ ላይ መሆኑን ኢዮአብ ሰማ፤ 2እንዲሁም ንጉሡ በልጁ ሞት ምክንያት በሐዘን ላይ መሆኑን ስለ ሰሙ ወታደሮቹ ያገኙት የድል አድራጊነት ደስታ በዚያ ቀን ወደ ሐዘን ተለወጠባቸው። 3ስለዚህ ከጦር ግንባር ተመልሰው ወደ ኋላ እንደሚሸሹ ወታደሮች ድምፃቸውን አጥፍተው በጸጥታ ወደ ከተማይቱ ገቡ፤ 4ንጉሡም ፊቱን ሸፍኖ “ልጄ ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! አቤሴሎም ልጄ!” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለቅስ ነበር።
5በዚህ ጊዜ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የቊባቶችህን ሕይወት ያዳኑትን ሰዎች ዛሬ አሳፍረሃቸዋል፤ 6አንተ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የሚጠሉህን ግን ትወዳለህ! ስለ ጦር መኰንኖችህና ስለ ወታደሮችህ ሁሉ ምንም የማይገድህ መሆኑን በግልጥ አሳይተሃል፤ አቤሴሎም በሕይወት ቢኖርና እኛ ሁላችን ብንጠፋ ኖሮ እጅግ እንደምትደሰት ተገንዝቤአለሁ፤ 7ይልቅስ አሁን ተነሥና ወታደሮችህን አበረታታ፤ ይህንን ባታደርግ ግን ነገ ጠዋት ከእነርሱ አንዱ እንኳ ከአንተ ጋር እንደማይሆን በእግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ይህም በሕይወትህ ከደረሰብህ መከራ ሁሉ እጅግ የከፋ ይሆንብሃል።” 8ከዚህ በኋላ ንጉሡ ከተቀመጠበት ተነሥቶ በመሄድ በከተማይቱ ቅጽር በር አጠገብ ተቀመጠ፤ ተከታዮቹም እዚያ መሆኑን ሰምተው ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ።
ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ጒዞ መጀመሩ
በዚህን ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ሸሽተው እያንዳንዱ ወደየቤቱ ሄዶ ነበር፤ 9በመላ አገሪቱም ሕዝቡ እርስ በርስ መጣላት ጀመረ፤ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ንጉሥ ዳዊት ከጠላቶቻችን እጅ አድኖናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አውጥቶናል፤ አሁን ግን ከአቤሴሎም ፊት በመሸሽ አገሪቱን ትቶ ሄዶአል። 10መሪያችን ይሆን ዘንድ አቤሴሎምን ቀብተን አንግሠነው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ በጦርነት ላይ ተገደለ፤ ታዲያ፥ ንጉሥ ዳዊትን መልሶ ለማምጣት የሚሞክር ሰው እንዴት ታጣ?”
11ንጉሥ ዳዊትም እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው የተናገሩትን ሰማ፤ ስለዚህም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን በመላክ የይሁዳን መሪዎች እንዲህ ብለው እንዲጠይቁአቸው አዘዘ፤ “ንጉሡን ረድታችሁ ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ ስለምን እናንተ የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ? 12እናንተ እኮ ለእኔ የሥጋ ዘመዶቼ ናችሁ፤ ታዲያ፥ እኔን መልሶ ለመውሰድ የመጀመሪያዎቹ በመሆን ፈንታ ስለምን የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ?” 13እንዲሁም ለዐማሳ ሲናገር “አንተም ለእኔ የሥጋ ዘመድ ነህ፤ ከአሁን ጀምሮ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ አደርግሃለሁ፤ ይህንንም ባላደርግ እግዚአብሔር በሞት ይቅጣኝ!” ብላችሁ ንገሩት ሲል አዘዛቸው። 14የዳዊት አነጋገር የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለእርሱ ታማኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው፤ ስለዚህም ከመኳንንቱ ሁሉ ጋር ተመልሶ እንዲመጣ ላኩበት።
15ዳዊት በመመለስ ላይ እንዳለም የይሁዳ ሰዎች እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ሄደው ተቀበሉት፤ አጅበውም ወንዙን ለማሻገር አስበው እስከ ጌልጌላ ድረስ መጡ፤ 16በዚያኑ ጊዜም የባሑሪም ተወላጅ የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሺምዒ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ፈጥኖ ሄደ፤ #2ሳሙ. 16፥5-13። 17ከእርሱም ጋር የብንያም ነገድ የሆኑ አንድ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳኦል ቤተሰብ አገልጋይ የነበረው ጺባም ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከኻያ አገልጋዮቹ ጋር መጣ፤ ወደ ዮርዳኖስም ወንዝ እየተጣደፉ ደርሰው በንጉሡ ፊት ቀረቡ። 18እነርሱም ንጉሡንና ተከታዮቹን በጀልባ አጅበው ወደ ማዶ ለማድረስና ንጉሡ የሚፈልገውን ሁሉ ለማድረግ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ።
ዳዊት ለሺምዒ ይቅርታ ማድረጉ
ንጉሡ ወንዙን ለመሻገር ሲዘጋጅ ሳለ የጌራ ልጅ ሺምዒ መጥቶ በፊቱ ተዘረጋና እንዲህ አለ፤ 19“ንጉሥ ሆይ! ከኢየሩሳሌም ወጥተህ በሄድክበት ቀን ያደረግኹትን በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ ቂም በቀልም አትያዝብኝ፤ ዳግመኛም ስለ እርሱ አታስብ፤ 20ጌታዬ ሆይ! ኃጢአት እንደ ሠራሁ ዐውቃለሁ፤ ዛሬ ግን ከሰሜን የእስራኤል ነገዶች የመጀመሪያው በመሆን አንተን ለመቀበል መጥቼአለሁ።”
21የጸሩያ ልጅ አቢሳም “እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠውን ስለተሳደበ ሺምዒ በሞት መቀጣት ይገባዋል” ሲል ተናገረ።
22ዳዊት ግን አቢሳንና ወንድሙን ኢዮአብን “ይህን አሳብ እንድታቀርቡ የጠየቃችሁ ማን ነው? ችግር ልታመጡብኝ ትፈልጋላችሁን? እነሆ፥ አሁን የእስራኤል ንጉሥ እኔ ነኝ፤ ደግሞም በዛሬው ዕለት ማንም እስራኤላዊ በሞት አይቀጣም” አላቸው። 23ሺምዒንም “በሞት እንደማትቀጣ ቃል እገባልሃለሁ!” አለው።
ዳዊት ለመፊቦሼት ይቅርታ ማድረጉ
24ከዚህ በኋላ የሳኦል የልጅ ልጅ መፊቦሼት ንጉሡን ለመቀበል ወረደ፤ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ አሁን በድል አድራጊነት እስከ ተመለሰበት ጊዜ ድረስ መፊቦሼት እግሩን አልታጠበም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም። #2ሳሙ. 9፥1-13፤ 16፥1-4። 25መፊቦሼት ከኢየሩሳሌም ተነሥቶ ንጉሡን በሚቀበልበት ስፍራ በደረሰ ጊዜ ንጉሡ “መፊቦሼት ሆይ፥ ስለምን ከእኔ ጋር ሳትሄድ ቀረህ?” አለው።
26መፊቦሼትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፥ እንደምታውቀው እኔ ሽባ ነኝ፤ ከአንተ ጋር ለመሄድ ፈልጌ አገልጋዬን ‘በቅሎዬን ጫንልኝ’ ብለው ከድቶኝ ሄደ፤ 27ንጉሥ ሆይ! እንዲያውም ስለ እኔ በውሸት ለአንተ የነገረህ ጉዳይ አለ፤ ነገር ግን አንተ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆንክ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ። 28ንጉሥ ሆይ! የአባቴ ቤተሰብ ሁሉ በሞት መቀጣት የሚገባው ነበር፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ግን በገበታህ ቀርቤ እንድመገብ መብት ሰጠኸኝ፤ ከዚህ የበለጠም ቸርነት እንዲደረግልኝ መጠየቅ አይገባኝም።”
29ንጉሡም “ከዚህ በላይ ብዙ መናገር አያስፈልግህም፤ አንተና ጺባ የሳኦል ንብረት ለሁለት እንድትካፈሉ ወስኛለሁ” ሲል መለሰ።
30መፊቦሼትም “ንጉሥ ሆይ! ሁሉንም ሀብት ጺባ ይውሰደው፤ ለእኔ አንተ በሰላም ወደ ቤትህ መመለስህ ብቻ ይበቃኛል” አለ።
ዳዊት ለባርዚላይ ቸርነት ማድረጉ
31ገለዓዳዊው ባርዚላይ ንጉሡን አጅቦ የዮርዳኖስን ወንዝ ለመሻገር ከሮገሊም መጣ፤ #2ሳሙ. 17፥27-29። 32ባርዚላይ ሰማኒያ ዓመት የሞላው ሽማግሌ ሰው ነበር፤ በጣም ሀብታም ከመሆኑም የተነሣ ንጉሥ ዳዊት በማሕናይም በነበረበት ጊዜ ይኸው ባርዚላይ ምግብ ያቀርብለት ነበር፤ 33ንጉሡም ባርዚላይ “ከእኔ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ና፤ እኔም በተድላና በደስታ እንድትኖር አደርግሃለሁ” አለው።
34ባርዚላይ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲያ ብዙ ዘመን አልኖርም፤ ታዲያ፥ ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ ምን ያስፈልገኛል? 35እነሆ፥ እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሰው ነኝ፤ የሚያስደስቱና የማያስደስቱ ነገሮችን መለየት እችላለሁን? የምበላውንም ሆነ የምጠጣውን ጣዕም መለየት እችላለሁን? ጆሮዬም የወንድና የሴት ዘፋኞችን ድምፅ መስማት ይችላልን? ንጉሥ ሆይ! በጌታዬ ላይ ለምን ተጨማሪ ሸክም እሆንብሃለሁ? 36ደግሞም ንጉሡ ይህን ያኽል ታላቅ ወሮታ የሚከፍለኝ ለምንድን ነው? ነገር ግን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሬ ከአንተ ጋር ጥቂት መንገድ ብቻ እሄዳለሁ። 37ከዚያም በኋላ እኔ አገልጋይህ ወደ ቤቴ ተመልሼ እንድሄድና በወላጆቼ መቃብር አጠገብ እንዳርፍ ፍቀድልኝ፤ እነሆ፥ ይህ ልጄ ኪምሀም ያገለግልሃል፤ ንጉሥ ሆይ! እርሱን ይዘኸው ሂድ፤ የወደድከውንም ለእርሱ አድርግለት።”
38ንጉሡም “እርሱን ይዤ እሄዳለሁ፤ እንዳደርግለት የምትፈልገውንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ለአንተም ቢሆን የምትጠይቀውን ሁሉ እፈጽማለሁ” አለው። 39ከዚህ በኋላ ዳዊትና ተከታዮቹ ሁሉ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ፤ ዳዊትም ባርዚላይን ሳመውና ባረከው፤ ባርዚላይም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ።
የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ስለ ንጉሥ ዳዊት መከራከራቸው
40ንጉሥ ዳዊት በይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በእስራኤል ሕዝብ እኩሌታ ታጅቦ ወንዙን ከተሻገረ በኋላ ወደ ጌልጌላ አቀና፤ ኪምሀምም አብሮት ተሻገረ፤ 41ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ ንጉሡ ቀርበው “ንጉሥ ሆይ! ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች አንተን ወስደው የራሳቸው ለማድረግ፥ እንዲሁም አንተንና ቤተሰብህን፥ ተከታዮችህንም ሁሉ አጅበው የዮርዳኖስን ወንዝ ለማሻገር መብት እንዳላቸው ስለምን ያስባሉ?” ሲሉ ጠየቁት።
42የይሁዳም ሰዎች “እኛ ይህን ያደረግነው ንጉሡ የእኛ ወገን ስለ ሆነ ብቻ ነው፤ ታዲያ፥ እናንተስ በዚህ ነገር ስለምን ትቈጣላችሁ? እርሱ ለምግባችን ምንም የከፈለን ነገር የለም፤ ሌላም ምንም ነገር አልሰጠንም” ሲሉ መለሱላቸው።
43እስራኤላውያንም “እርሱ የእናንተ ወገን ቢሆንም እንኳ እናንተ ከምትፈልጉት ይበልጥ እኛ እንፈልገዋለን፤ ከመንግሥቱ ዐሥሩ እጅ የሚገባው ለእኛው ነው፤ እናንተ እኛን የምትንቁት ስለምንድን ነው? ንጉሡን ስለ መመለስ በመጀመሪያ ጥያቄ ያቀረብነው እኛ መሆናችንን ልትዘነጉ አይገባም!” አሉአቸው።
ነገር ግን ከእስራኤል ሰዎች ይልቅ የይሁዳ ሰዎች ዳዊትን የራሳቸው ለማድረግ በብርቱ ተከራከሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ