የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20

20
ሼባዕ የፈጸመው ዐመፅ
1በዚያን ጊዜ ሼባዕ ተብሎ የሚጠራ ጠባዩ የተበላሸ የማይረባ አንድ ሰው በጌልገላ ይኖር ነበር፤ እርሱም ትውልዱ ከብንያም ነገድ ሲሆን አባቱ ቢክሪ ይባላል፤ ይህም ሼባዕ እምቢልታ ነፍቶ “ከዳዊት ጋር ምንም ድርሻ የለንም! ከእሴይ ልጅ ጋር ምንም ዕድል ፈንታ የለንም! የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እያንዳንድህ ወደ ቤትህ ግባ!” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ። #1ነገ. 12፥16፤ 2ዜ.መ. 10፥16። 2ስለዚህም እስራኤላውያን ዳዊትን ከድተው ከሼባዕ ጋር ሄዱ፤ የይሁዳ ሕዝብ ግን ታማኝነታቸውን በማጽናት ከዮርዳኖስ እስከ ኢየሩሳሌም ዳዊትን ተከትለው ሄዱ።
3ዳዊት በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መንግሥቱ በደረሰ ጊዜ፥ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁለት ትቶአቸው የነበሩትን ዐሥር ቊባቶቹን ወደ ሌላ ወስዶ በዘበኛ እንዲጠበቁ አደረገ፤ የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እንዲሰጣቸው አዘዘ፤ ይሁን እንጂ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት አልፈጸመም፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው በቤት ተወስነው እንደ መበለቶች በመሆን ኖሩ። #2ሳሙ. 16፥22።
4ንጉሡም ዐማሣን “የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠርተህ በአንድነት ሰብስብና ከነገ ወዲያ ይዘሃቸው ወደዚህ ተመለስ” አለው። 5ዐማሣም ሊጠራቸው ሄደ፤ ነገር ግን ንጉሡ በቀጠረው ቀን ተመልሶ ሊመጣ አልቻለም። 6ስለዚህ ንጉሡ አቢሳን “ሼባዕ ከአቤሴሎም ይበልጥ የከፋ ችግር ይፈጥርብናል፤ ወታደሮቼን ይዘህ ተከታተለው፤ አለበለዚያ የተመሸጉ ከተሞቼን ይዞ ከእኛ እጅ ሊያመልጥ ይችላል” አለው። 7ስለዚህ የኢዮአብ ወታደሮች፥ የንጉሡ የክብር ዘበኞችና ሌሎች ወታደሮችም ከአቢሳ ጋር ከኢየሩሳሌም ወጥተው የቢክሪን ልጅ ሼባዕን በመከታተል አሳደዱት። 8በገባዖን ወደሚገኘው ወደ ትልቁ ድንጋይ በደረሱ ጊዜ ዐማሣ አገኛቸው፤ በዚህን ጊዜ ኢዮአብ ሰይፉን በሰገባው ከቶ፥ ሰገባውንም በመታጠቂያው ላይ አስሮ ለጦርነት ተዘጋጅቶ ነበር፤ እየተራመደ ወደ ፊት ሲሄድ ሳለም ሰይፉ ወደቀ፤ 9ኢዮአብም ዐማሣን “ወዳጄ ሆይ! እንደምንድን ነህ?” አለውና የሚስመው በማስመሰል ሪዙን በቀኝ እጁ ያዘ፤ 10ኢዮአብ በሌላው እጁ የያዘውን ሰይፍ ስላላየ ዐማሣ አልተጠነቀቀም ነበርና ኢዮአብ በሆዱ ሻጠበት፤ የሆድ ዕቃውም መሬት ላይ ተዘረገፈ፤ ወዲያውኑ ስለ ሞተም ኢዮአብ በድጋሚ አልወጋውም።
ከዚህ በኋላ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ የቢክሪን ልጅ ሼባዕን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ። 11ከኢዮአብ ወታደሮች አንዱ በዐማሳ ሬሳ አጠገብ ቆሞ “ኢዮአብንና ዳዊትን የምትከተሉ ሁሉ ኢዮአብን ተከተሉ!” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ። 12የዐማሳ ሬሳ በደም እንደ ተበከለ በመንገዱ መካከል ተዘርሮ ነበር፤ ያም ሰው የኢዮአብ ወታደር ሁሉ ቆሞ ሲመለከት አይቶ ሬሳውን በመጐተት ወደ እርሻ ወሰደውና በልብስ ሸፈነው። #20፥12 በደም ተበከለ፦ በዕብራይስጡ ተንከባለለ ይላል። 13ሬሳው ከመንገዱ መካከል ከተነሣ በኋላ ሰዎች ሁሉ የቢክሪን ልጅ ሼባዕን ለማሳደድ ኢዮአብን ተከትለው ሄዱ።
14ሼባዕ በእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ አልፎ በመሄድ አቤልቤትማዕካ ወደተባለች ከተማ ደረሰ፤ የቢክሪ ጐሣ አባሎች የሆኑ ሁሉ ተሰብስበው ሼባዕን በመከተል ወደ ከተማይቱ ገቡ፤ 15የኢዮአብ ወታደሮች ሼባዕ እዚያ መሆኑን ስለ ሰሙ ሄደው ከተማይቱን ከበቡ፤ በስተውጪ በኩል ቅጽሩን አስደግፈው የዐፈር ቊልል ሠሩ፤ ቀጥሎም ቅጽሩ እንዲወድቅ ከስሩ መቈፈር ጀመሩ። 16በከተማይቱ ውስጥ የምትኖር አንዲት ብልኅ ሴት በቅጽሩ ላይ ሆና ድምፅዋን ከፍ በማድረግ “ስሙ! ስሙ! ኢዮአብ ወደዚህ ይመጣ ዘንድ ንገሩት፤ እኔ ላነጋግረው እፈልጋለሁ!” አለች። 17ኢዮአብ ወደዚያ በሄደ ጊዜም ሴትዮዋ “ኢዮአብ የምትባለው አንተ ነህን?” ስትል ጠየቀችው።
እርሱም “አዎ እኔ ነኝ” አላት።
እርስዋም “ጌታዬ፥ እስቲ አድምጠኝ” አለችው፤
እርሱም “እነሆ፥ አዳምጥሻለሁ” አላት።
18እርስዋም እንዲህ አለችው፤ “በድሮ ዘመን ‘ወደ አቤል ከተማ ሄዳችሁ የጥያቄአችሁን መልስ ከዚያ ታገኛላችሁ’ ይባል ነበር፤ ሰዎችም የሚያደርጉት ይህንኑ ነበር። 19የእኔ ከተማ ግን ታላቅ ከተማ ናት፤ በእስራኤል ሰላም የሰፈነባትና ታማኝ ከተማ እርስዋ ናት፤ ታዲያ፥ አንተ ይህችን ከተማ ለመደምሰስ ለምን ታቅዳለህ? የእግዚአብሔር ርስት የሆነውን ነገር ለማፍረስ ትፈልጋለህን?”
20ኢዮአብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ከተማችሁን አልደመስስም! ከቶም አላፈርስም! 21የእኛ ዕቅድ ይህ አይደለም፤ የተራራማው የኤፍሬም አገር ተወላጅ የሆነ ሼባዕ ተብሎ የሚጠራ የቢክሪ ልጅ በንጉሥ ዳዊት ላይ ዐመፅ አስነሥቶአል፤ ብቻ ይህ ሰው ይሰጠኝ እንጂ እኔ ከተማይቱን ለቅቄ እሄዳለሁ።”
እርስዋም “ራሱን ቈርጠን በግንብ ላይ እንወረውርልሃለን” አለችው። 22ይህንንም ዕቅድ በተግባር ለመግለጥ ወደ ከተማይቱ ሕዝብ ሄደች፤ እነርሱም የቢክሪን ልጅ የሺባዕን ራስ ቈርጠው በግንቡ ላይ ለኢዮአብ ወረወሩለት፤ እርሱም ወታደሮቹ ከተማይቱን ለቀው ይወጡ ዘንድ ምልክት እንዲሆን እምቢልታ ነፋ፤ እነርሱም ወደየቤታቸው ተመለሱ፤ ኢዮዓብም ንጉሡን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ።
የዳዊት ባለሟሎች
23ኢዮአብ የእስራኤል ሠራዊት አዛዥ ሲሆን፥ የዮዳሄ ልጅ በናያ የዳዊት ክብር ዘብ ኀላፊ ነበር፤ 24አዶኒራም ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ገባሮች ኀላፊ ሲሆን፥ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበር፤ 25ሱሳ የቤተ መንግሥት ጸሐፊ ሲሆን፥ ሳዶቅና አብያታር ካህናት ነበሩ፤ 26እንዲሁም የያዒር ከተማ ተወላጅ የሆነው ዒራ ከዳዊት ካህናት አንዱ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ