የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21

21
የሳኦል ዘሮች በሞት መቀጣት
1በዳዊት ዘመነ መንግሥት ሦስት ዓመት ሙሉ ጽኑ ራብ ነበር፤ ዳዊትም ስለዚህ ጉዳይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጠየቀ ጊዜ እግዚአብሔር “ሳኦልና ቤተሰቡ ግድያ በመፈጸም በደል ሠርተዋል፤ ሳኦልም የገባዖንን ሰዎች ፈጅቶአል” ሲል መለሰለት። 2እንደሚታወቀው ሁሉ የገባዖን ሰዎች እስራኤላውያን አልነበሩም፤ እነርሱ እስራኤላውያን ሊጠብቁአቸው ቃል ስለ ገቡላቸው ከአሞራውያን ተከፍለው ብቻቸውን የሚኖሩ ነበሩ፤ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ በነበረው ቀኖች ሊያጠፋቸው ዐቅዶ ነበር። #ኢያሱ 9፥3-15። 3ስለዚህም ዳዊት የገባዖንን ሰዎች በአንድነት ጠርቶ “የእግዚአብሔርን ሕዝብ ትመርቁ ዘንድ ቀድሞ በተፈጸመባችሁ ግፍ ፈንታ ካሣ የሚሆን አንድ ነገር ላደርግላችሁ እፈልጋለሁ፤ ታዲያ፥ ምን ላድርግላችሁ?” አላቸው።
4እነርሱም “ከሳኦልና ከቤተሰቡ ጋር ያለን ጥል በብርና በወርቅ የሚገታ አይደለም፤ ከዚህም በቀር እኛ ከእስራኤል ወገን ማንንም መግደል አንፈልግም” ሲሉ መለሱለት።
ዳዊትም “ታዲያ ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
5እነርሱም “ሳኦል በሙሉ ሊያጠፋንና ከእኛ መካከል ማንም ሰው በእስራኤል ምድር በየትኛውም ስፍራ በሕይወት እንዳይኖር ፈልጎ ነበር፤ 6ስለዚህ ከሳኦል ዘሮች ሰባት ወንዶችን ለእኛ አሳልፈህ ስጠን፤ እኛም እነርሱን እግዚአብሔር መርጦ ባነገሠው በንጉሥ ሳኦል ከተማ በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንሰቅላቸዋለን” ሲሉ መለሱ።
ንጉሥ ዳዊትም “እነርሱን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው።
7ነገር ግን ዳዊትና ዮናታን እርስ በርሳቸው በገቡት የተቀደሰ ቃል ኪዳን ምክንያት ዳዊት የሳኦልን የልጅ ልጅ የዮናታንን ልጅ መፊቦሼትን አሳልፎ አልሰጣቸውም። #1ሳሙ. 20፥15-17፤ 2ሳሙ. 9፥1-7። 8ይሁን እንጂ ዳዊት የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች አርሞኒንና መፊቦሼትን ወሰደ፤ እንዲሁም የሳኦል ልጅ ሜራብ የመሖላን ተወላጅ ለሆነው ለባርዚላይ ልጅ ለዐድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጨምሮ ወሰደ። #1ሳሙ. 18፥19። 9ዳዊት እነዚህን ሁሉ ለገባዖን ሰዎች አሳልፎ ሰጠ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፤ ሰባቱም በአንድነት ሞቱ፤ እነርሱም የተገደሉት በጸደይ ወራት ማለቂያና በገብስ መከር መጀመሪያ ላይ ነበር።
10ከዚህ በኋላ የሳኦል ቊባት የነበረችው የአያ ልጅ ሪጽፋ ሬሳዎቹ ባሉበት ስፍራ አጠገብ በሚገኘው ቋጥኝ ድንጋይ ላይ ማቅ ዘርግታ ከስሩ ተቀመጠች፤ እርስዋም ከመከር ጊዜ መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ እስከሚጥልበት ጊዜ ድረስ እዚያ ቈየች፤ ቀን ቀን ወፎች በሬሳዎቹ ላይ እንዳያርፉ እየተከላከለች፥ ሌሊት ሌሊትም አውሬ እንዳይበላቸው ትጠብቃቸው ነበር።
11ዳዊት፥ የሳኦል ቁባት የነበረችው ሪጽፋ ያደረገችውን በሰማ ጊዜ፥ 12በገለዓድ ምድር ወደምትገኘው ወደ ያቤሽ ሕዝብ ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም አመጣ፤ የያቤሽ ሕዝብ ዐፅሙን ያገኙት ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ በገደሉበት ቀን ሬሳዎችን ከሰቀሉበት ከቤትሻን አደባባይ በመስረቅ ነበር። #1ሳሙ. 31፥8-13። 13ዳዊት የሳኦልንና የዮናታንን ዐፅም ወሰደ፤ እንዲሁም ተሰቅለው የነበሩትን የሰባቱን ሰዎች አስከሬን ሰበሰበ፤ 14ከዚህ በኋላ የሳኦልንና የዮናታንን ዐፅም ወስደው በብንያም ጼላዕ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ውስጥ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ቀበሩ፤ ይህ ሁሉ ከተፈጸመም በኋላ ሕዝቡ ስለ አገራቸው ያቀረቡትን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።
ከፍልስጥኤማውያን ኀያላን ጋር የተደረገ ጦርነት
(1ዜ.መ. 20፥4-8)
15በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤላውያን መካከል የተደረገ ሌላም ጦርነት ነበር፤ ስለዚህም ዳዊትና ተከታዮቹ ዘምተው ፍልስጥኤማውያንን ወጉ፤ ከውጊያዎቹም በአንዱ ዳዊት ደክሞት ነበር፤ 16ሦስት ኪሎ ተኩል የሚመዝን ከነሐስ የተሠራ ጦር የያዘና አዲስ ሰይፍ የታጠቀ ዩሽቢበኖብ ተብሎ የሚጠራ አንድ ኀያል ሰው ዳዊትን ለመግደል አስቦ ነበር፤ 17ነገር ግን የጸሩያ ልጅ አቢሳ ዳዊትን ለመርዳት መጥቶ በዚያ ኀያል ሰው ላይ አደጋ በመጣል ገደለው፤ ከዚያን በኋላ የዳዊት ተከታዮች ዳግመኛ ከእነርሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄድ ዳዊትን ቃል በማስገባት “የእስራኤል መብራት የሆንክ አንተ እንዳትጠፋ ዳግመኛ ወደ ጦርነት አትወጣም” አሉ። #1ነገ. 11፥36፤ መዝ. 132፥17።
18ከዚህ በኋላ ጎብ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጦርነት ተደረገ፤ በዚህን ጊዜ የሑሻ ተወላጅ የሆነው ሲበካይ፥ ሳፍ ተብሎ የሚጠራውን ከራፋይም ወገን የነበረውን ኀያል ሰው ገደለ።
19ቀጥሎም በጎብ ሌላ ጦርነት ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተደረገ፤ በዚህም ጊዜ የቤተልሔም ተወላጅ የሆነው የያዒር ልጅ ኤልሐናን የጋት ተወላጅ የሆነውንና የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን ጎልያድ ተብሎ የሚጠራውን ሌላ ፍልስጥኤማዊ ገደለ።
20ከዚህም በኋላ በጋት ላይ ጦርነት ተደረገ፤ በዚያም ጦርነት የሚወድ አንድ ኀያል ሰው ነበረ፤ ያም ኀያል ሰው በእጆቹና በእግሮቹ ስድስት ስድስት ጣቶች ነበሩት፤ እርሱም ከራፋይም የተወለደ ነበር። 21እርሱም እስራኤላውያንን በብርቱ ተፈታተነ፤ ይሁን እንጂ እርሱን የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናታን ገደለው።
22እነዚህ አራቱ የጋት ኀያላን ሰዎች የራፋይም ዘሮች ሲሆኑ ሁሉንም ዳዊትና አገልጋዮቹ ገደሉአቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ