የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17

17
የሑሻይ አቤሴሎምን ማዘናጋት
1ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቈይ አኪጦፌል አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ዛሬ ማታ ዳዊትን አሳድጄ ለመያዝ እችል ዘንድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች እንድመርጥ ፍቀድልኝ፤ 2ደክሞት ተስፋ በመቊረጥ ላይ ሳለ ድንገተኛ አደጋ እጥልበታለሁ፤ በዚያን ጊዜ እርሱ ድንጋጤ ላይ ይወድቃል፤ ተከታዮቹም ጥለውት ይሸሻሉ ንጉሡንም ለብቻው አግኝቼ እገድለዋለሁ፤ 3ሙሽራ ወደ ባልዋ እንደምትመለስ ተከታዮቹ በሙሉ ወደ አንተ ተመልሰው እንዲመጡ አደርጋለሁ፤ እንግዲህ አንተ የምትፈልገው አንድ ሰው ብቻ መግደልን ነው፤ የቀረው ሌላው ሕዝብ ግን በሰላም ይኖራል።” 4ይህም ለአቤሴሎምና ለእስራኤል መሪዎች ሁሉ ጥሩ ምክር መስሎ ታያቸው።
5አቤሴሎምም “አሁን ደግሞ አርካዊውን ሑሻይን ጥሩትና እርሱ የሚለውን እንስማ” አለ። 6ሑሻይም በደረሰ ጊዜ አቤሴሎም “አኪጦፌል የሰጠን ምክር ይህ ነው፤ ይህንኑ ምክር እንከተል ወይስ ምን ማድረግ እንደሚገባን አንተም የምትነግረን አለ ይሆን?” ሲል ጠየቀው።
7ሑሻይም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በአሁኑ ሰዓት አኪጦፌል የሰጣችሁ ምክር ጥሩ አይደለም፤ 8አባትህ ዳዊትና ተከታዮቹ ብርቱ ጦረኞች እንደሆኑና ግልገሎችዋ እንደ ተነጠቁባትም ድብ አስፈሪዎች መሆናቸውን ታውቃለህ፤ አባትህ በጦር ልምድ የተፈተነ ወታደር በመሆኑ ሌሊቱን ከሠራዊቱ ጋር አያድርም፤ 9ምናልባት አሁን እንኳ በዋሻ ውስጥ ወይም በሌላ ስፍራ ተሸሽጎ ሊሆን ይችላል፤ ዳዊት በአንተ ሠራዊት ላይ አደጋ እንደ ጣለባቸው የሚሰማ ሰው ሁሉ ወዲያውኑ ወታደሮችህ እንደ ተሸነፉ አድርጎ ያወራል። 10አባትህ ታላቅ ጦረኛ መሆኑንና የእርሱም ተከታዮች ብርቱ ተዋጊዎች መሆናቸውን በእስራኤል የሚኖር ሁሉ ስለሚያውቅ እንደ አንበሳ ደፋሮች የሆኑት ወታደሮችህ እንኳ ልባቸው በፍርሃት ሊቀልጥ ይችላል። 11ስለዚህ እኔ የምመክርህ፥ ከአገሪቱ አራት ማእዘኖች ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉትንና ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የሆነው እስራኤላውያን ሁሉ በአንድነት ሰብስበህ አንተው ራስህ አዛዥ በመሆን ወደ ጦርነቱ እንድትመራቸው ነው። 12የትም ስፍራ ቢደበቅ ዳዊትን ፈልገን እናገኘዋለን፤ በረዶ በምድር ላይ እንደሚወርድ እንወርድበታለን፤ እርሱም ሆነ ከተከታዮቹ አንድ ሰው እንኳ በሕይወት የሚተርፍ አይኖርም። 13ሸሽቶ ወደ ከተማም ቢገባ ሕዝባችን በሙሉ ገመድ አምጥተው ከተማይቱን በመሳብ በእርስዋ ሥር ወደሚገኘው ሸለቆ አሽቀንጥረው ይጥሉአታል፤ በኮረብታውም ላይ አንድ ድንጋይ እንኳ አይቀርም።”
14አቤሴሎምና እስራኤላውያን በሙሉ “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የሑሻይ ምክር ይበልጣል” አሉ፤ በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ይመጣበት ዘንድ እግዚአብሔር የአኪጦፌል መልካም ምክር ተቀባይ እንዳይኖረው አደረገ።
የዳዊት ማምለጥ
15ከዚህ በኋላ እርሱና አኪጦፌል ለአቤሴሎምና ለእስራኤላውያን መሪዎች የሰጡትን ምክር ሑሻይ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ነገራቸው፤ 16ከዚህም ጋር “እንግዲህ ዛሬ ሌሊት በበረሓ ውስጥ በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ ላይ እንዳያድር በፍጥነት መልእክተኛ ልካችሁ ለዳዊት ንገሩት! ነገር ግን እርሱና ተከታዮቹ ተይዘው እንዳይገደሉ በፍጥነት የዮርዳኖስን ወንዝ ይሻገሩ!” አላቸው።
17የአብያታር ልጅ ዮናታንና የሳዶቅ ልጅ አሒማዓጽ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ማንም እንዳያያቸው ስለ ፈሩ፥ ከኢየሩሳሌም አካባቢ ባለችው በዔንሮጌል ምንጭ አጠገብ ይጠባበቁ ነበር፤ አንዲት ልጃገረድ አገልጋይም ዘወትር ወደዚያ እየሄደች የሚሆነውን ነገር ሁሉ ትነግራቸው ነበር፤ ከዚያም በኋላ እነርሱ ሄደው ለንጉሥ ዳዊት ይነግሩት ነበር። 18ነገር ግን አንድ ቀን አንድ ልጅ እነርሱን ስላያቸው ሄዶ ለአቤሴሎም ነገረው፤ ስለዚህ እነርሱ በባሑሪም በሚገኘው በአንድ ሰው ቤት ለመሸሸግ ሮጠው ሄዱ፤ ሰውየው በቤቱ አጠገብ የውሃ ጒድጓድ ስለ ነበረው ወደዚያ ውስጥ ገቡ። 19የዚያም ሰው ሚስት ጒድጓዱን ሸፍና በላዩ ላይ ማንም ሰው እንዳይጠረጥር እህል አሰጣችበት። 20የአቤሴሎም ባለሟሎች ወደዚያ ቤት መጥተው ሴቲቱን “አሒማዓጽና ዮናታን የት ናቸው?” ሲሉ ጠየቁአት።
እርስዋም “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል” ስትል መለሰች።
ሰዎቹም ፈልገው ሊያገኙአቸው ስላልቻሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 21እነርሱም ከሄዱ በኋላ አሒማዓጽና ዮናታን በፍጥነት ከጒድጓዱ ወጥተው በመሄድ የሆነውን ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ነገሩት፤ አኪጦፌል በእነርሱ ላይ ዐቅዶት የነበረውን ካስረዱት በኋላም “ፈጥነህ ወንዙን ተሻገር!” አሉት። 22ስለዚህም ዳዊትና ተከታዮቹ የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር ጀመሩ፤ እስኪነጋም ድረስ ሁሉም ወንዙን ተሻግረው ነበር።
23አኪጦፌል የሰጠው ምክር ተቀባይነት እንዳላገኘ በተረዳ ጊዜ አህያውን ጭኖ ወደ መኖሪያ ከተማው ተመልሶ ሄደ፤ ሁሉን ነገር መልክ በማስያዝ ካስተካከለም በኋላ ተሰቅሎ ሞተ፤ በቤተሰቡም መቃብር ተቀበረ።
24አቤሴሎምና እስራኤላውያን ሁሉ የዮርዳኖስን ወንዝ በተሻገሩ ጊዜ ዳዊት ማሕናይም ተብላ ወደምትጠራው ትንሽ ከተማ ደርሶ ነበር፤ 25አቤሴሎም በኢዮአብ ምትክ ዐማሣ ተብሎ የሚጠራውን ሰው የጦር አዛዥ አድርጎ ሾመ፤ ዐማሣ የእስራኤላዊው የዬቴር ልጅ ነበር፤ እናቱም አቢጌል ተብላ የምትጠራ የናሐሽ ልጅ ስትሆን ለኢዮአብ እናት ለጸሩያ እኅት ነበረች። #17፥25 እስራኤላዊ፦ በሌሎች እስማኤላዊ ተብሎ ይገኛል። ዜና መ. 2፥17 26አቤሴሎምና ሠራዊቱም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ።
27ዳዊት ማሕናይም በደረሰ ጊዜ በዐሞን ግዛት ራባ ተብላ ከምትጠራው ከተማ የመጣውን የናዖስን ልጅ ሾቢን፥ ከሎደባር ከተማ የመጣውን የዓሚኤልን ልጅ ማኪርንና ከገለዓድ ግዛት ሮገሊም ተብላ ከምትጠራው ከተማ የመጣውን ባርዚላይን አገኘ። 28-29እነርሱም ምንቸቶችንና የሸክላ ማሰሮዎችን፥ የመኝታ አልጋዎችንም ይዘው መጡ፤ እንዲሁም ለዳዊትና ለተከታዮቹ የሚሆን ስንዴ፥ ገብስ፥ ዱቄት፥ የተጠበሰ እሸት፥ ባቄላ፥ አተር፥ ማር፥ አይብ፥ እርጎና በጎችን አመጡ፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት ዳዊትና ተከታዮቹ በበረሓ ኑሮ እንደሚርባቸው፥ እንደሚጠማቸውና እንደሚደክማቸው በማሰብ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ