የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 11

11
የይሁዳ ንግሥት ዐታልያ (ጎቶሊያ)
(2ዜ.መ. 22፥10—23፥15)
1የንጉሥ አካዝያስ እናት ዐታልያ የልጅዋን መገደል እንደ ሰማች ወዲያውኑ የይሁዳ ንጉሣውያን ቤተሰብ አባላት በሙሉ እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጠች። 2ከእርስዋም እጅ ማምለጥ የቻለ የአካዝያስ ልጅ ኢዮአስ ብቻ ነበር፤ እርሱም እንኳ ከሌሎቹ ጋር እንዲገደል ተመክሮበት ነበር፤ ነገር ግን አክስቱ የነበረችው በአባትዋ በኩል የንጉሥ አካዝያስ እኅት የሆነችው፥ የንጉሥ ኢዮራም ልጅ ይሆሼባዕ በመደበቅ ከሞት አዳነችው፤ እርስዋም እርሱንና ሞግዚቱን ወስዳ በቤተ መቅደሱ ግቢ በሚገኘው ማረፊያ ክፍል ውስጥ ስለ ደበቀችው በዐታልያ እጅ ሳይገደል ቀረ። 3ዐታልያ በነገሠችበትም ስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ፥ ይሆሼባዕ ሕፃኑን ኢዮአስን በቤተ መቅደስ በመንከባከብ አሳደገችው።
4ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ለንጉሡ ክብር ዘቦችና ለቤተ መንግሥቱ ጠባቂዎች ሁሉ ኀላፊዎች ወደሆኑት የጦር መኰንኖች ሁሉ ልኮ ወደ ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አስጠራቸው፤ በዚያም ሊያደርገው ያቀደውን ይስማሙበት ዘንድ በመሐላ እንዲያረጋግጡለት አደረገ፤ ከዚያም በኋላ የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን አሳያቸውና፥ 5የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “በሰንበት ቀን ለዘብ ጥበቃ በምትሰማሩበት ጊዜ ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤ 6ሌላው አንድ ሦስተኛ እጅ የሱርን የቅጽር በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሦስተኛ እጅ ደግሞ ከሌሎቹ ዘቦች በስተኋላ ያለውን ቅጽር በር ይጠብቅ። 7በሰንበት ቀን ከዘብ ጥበቃ ነጻ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ግን በንጉሡ ላይ አደጋ እንዳይደርስበት ለመከላከል ቤተ መቅደሱን ይጠብቁ፤ 8ንጉሥ ኢዮአስን በዙሪያው በምትጠብቁበትም ጊዜ ሰይፋችሁን መዛችሁ ወደሚሄድበት ስፍራ ሁሉ አብራችሁ ሂዱ፤ ወደ እናንተ ለመቅረብ የሚደፍር ማንም ቢኖር ይገደል።”
9የጦር መኰንኖቹም ዮዳሄ የሰጠውን መመሪያ በመቀበል በሰንበት ቀን ለዘብ ጥበቃ የሚሰማሩትንና ከዘብ ጥበቃም የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ጭምር አሰልፈው ወደ እርሱ አመጡ። 10ዮዳሄም በቤተ መቅደስ ተቀምጠው ይጠበቁ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮችና ጋሻዎች አውጥቶ ለጦር አለቆቹ ሰጣቸው፤ 11ጭፍሮቹም ሰይፋቸውን እንደ መዘዙ ንጉሡን ከአደጋ ለመከላከል በመሠዊያው በኩል በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ዙሪያውን እንዲሰለፉ አደረጋቸው። 12ከዚያም በኋላ ዮዳሄ ኢዮአስን አውጥቶ በራሱ ላይ ዘውድ ጫነበት፤ ለመንግሥቱ መመሪያ የሆነውንም ሕግ አንድ ቅጂ አስረከበው፤ በዚህ ዐይነት ኢዮአስ ተቀብቶ ነገሠ፤ ሕዝቡም እያጨበጨበ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ!” አለ።
13ንግሥት ዐታልያም የክብር ዘቦቹንና የሕዝቡን ጩኸት ድምፅ በሰማች ጊዜ ሕዝቡ ወደተሰበሰበበት ቤተ መቅደስ ፈጥና ሄደች። 14እዚያም እንደ ደረሰች አዲሱ ንጉሥ በተለመደው ባህል መሠረት በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሚገኘው ዐምድ አጠገብ ቆሞ አየችው፤ እርሱም በጦር አዛዦችና በእምቢልታ ነፊዎች ታጅቦ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በደስታ ተሞልተው እልል እያሉ እምቢልታ ይነፉ ነበር፤ ዐታልያም በድንጋጤ ልብስዋን ቀዳ “ይህ በክሕደት የተፈጸመ ሤራ ነው! ሤራ ነው!” ስትል ጮኸች። #2ነገ. 23፥3።
15ዮዳሄ በበኩሉ ዐታልያ በቤተ መቅደሱ ክልል ውስጥ እንድትገደል አልፈለገም፤ ስለዚህም የጦር አለቆቹን “ግራና ቀኝ በተሰለፉት ዘቦች መካከል አውጥታችሁ ውሰዱአት፤ እርስዋን ለመከተል የሚሞክር ቢኖር ይገደል” ሲል አዘዛቸው። 16እነርሱም እርስዋን አፈፍ አድርገው በመያዝ ወደ ቤተ መንግሥት ወሰዱአት፤ እዚያም የፈረስ መግቢያ ቅጽር በር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ገደሉአት።
ዮዳሄ ያደረገው ተሐድሶ
(2ዜ.መ. 23፥16-21)
17ዮዳሄ፥ ንጉሡና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ፤ እንዲሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ። 18ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ወደ ባዓል ቤተ መቅደስ ሄዶ አፈራረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበረ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የባዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደለው።
ዮዳሄ ቤተ መቅደሱን በየተራ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ፤ 19ከዚህም በኋላ እርሱ፥ የጦር አለቆች፥ የንጉሡ ክብር ዘብና የቤተ መንግሥቱ ዘብ ጠባቂዎች ንጉሡን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት አጅበው እንዲሄዱና ሕዝቡም ሁሉ ከኋላ እንዲከተል አደረገ፤ ኢዮአስም በዘብ ጠባቂዎች ቅጽር በር በኩል ገብቶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ። 20ዐታልያ ስለ ተገደለች ሰው ሁሉ ተደሰተ፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች።
21ኢዮአስም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ