ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉት አብያተ ክርስቲያን የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንወዳለን። እነርሱ በብዙ መከራ ተፈትነዋል፤ ይሁን እንጂ ደስታቸው ታላቅ ነበር፤ በጣም ድኾች ቢሆኑም እንኳ ከፍ ያለ ልግሥና አድርገዋል። የሚቻላቸውን ያኽልና ከሚቻላቸውም በላይ በፈቃደኛነት እንደ ሰጡ እኔ እመሰክርላቸዋለሁ፤ በይሁዳ ያሉትን ክርስቲያኖች የመርዳት ዕድል እንዳይነፈጋቸውም አጥብቀው ለመኑን፤ እነርሱ ያደረጉት እኛ ከጠበቅነው በላይ ነው፤ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥሎም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጥተዋል። ይህን ሥራ አስቀድሞ የጀመረው ቲቶ ስለ ነበረ አሁንም ይህንኑ የልግሥና ሥራችሁን ወደ ፍጻሜ እንዲያደርስ እርሱኑ ለምነነዋል። እናንተ በእምነት፥ በንግግር፥ በዕውቀት፥ በትጋት፥ ለእኛም ባላችሁ ፍቅር በሁሉ ነገር ትበልጣላችሁ፤ በዚህ በልግሥና ሥራም እንድትበልጡ ይሁን። ታዲያ፥ ይህን የምላችሁ በማዘዝ አይደለም፤ ነገር ግን የሌሎችን የመስጠት ትጋት ከእናንተ ትጋት ጋር በማወዳደር የእናንተን ፍቅር እውነተኛነት ለማረጋገጥ ብዬ ነው። እናንተ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁ፤ እርሱ ምንም እንኳ ሀብታም ቢሆን በእርሱ ድኻ መሆን እናንተ ሀብታሞች እንድትሆኑ ስለ እናንተ ብሎ ድኻ ሆነ።
2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8:1-9
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos