2 ቆሮንቶስ 8:1-9
2 ቆሮንቶስ 8:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉት አብያተ ክርስቲያን የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንወዳለን። እነርሱ በብዙ መከራ ተፈትነዋል፤ ይሁን እንጂ ደስታቸው ታላቅ ነበር፤ በጣም ድኾች ቢሆኑም እንኳ ከፍ ያለ ልግሥና አድርገዋል። የሚቻላቸውን ያኽልና ከሚቻላቸውም በላይ በፈቃደኛነት እንደ ሰጡ እኔ እመሰክርላቸዋለሁ፤ በይሁዳ ያሉትን ክርስቲያኖች የመርዳት ዕድል እንዳይነፈጋቸውም አጥብቀው ለመኑን፤ እነርሱ ያደረጉት እኛ ከጠበቅነው በላይ ነው፤ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥሎም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጥተዋል። ይህን ሥራ አስቀድሞ የጀመረው ቲቶ ስለ ነበረ አሁንም ይህንኑ የልግሥና ሥራችሁን ወደ ፍጻሜ እንዲያደርስ እርሱኑ ለምነነዋል። እናንተ በእምነት፥ በንግግር፥ በዕውቀት፥ በትጋት፥ ለእኛም ባላችሁ ፍቅር በሁሉ ነገር ትበልጣላችሁ፤ በዚህ በልግሥና ሥራም እንድትበልጡ ይሁን። ታዲያ፥ ይህን የምላችሁ በማዘዝ አይደለም፤ ነገር ግን የሌሎችን የመስጠት ትጋት ከእናንተ ትጋት ጋር በማወዳደር የእናንተን ፍቅር እውነተኛነት ለማረጋገጥ ብዬ ነው። እናንተ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁ፤ እርሱ ምንም እንኳ ሀብታም ቢሆን በእርሱ ድኻ መሆን እናንተ ሀብታሞች እንድትሆኑ ስለ እናንተ ብሎ ድኻ ሆነ።
2 ቆሮንቶስ 8:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እነግራችኋለሁ። በብዙ መከራ ከመፈተናቸው የተነሣ ደስታቸው በዝቶአልና፤ በድህነታቸው ጥልቅነትም የለጋስነታቸው ባለጠግነት በዝታለችና። እነርሱ ሲቻላቸው፥ ሳይቻላቸውም እንስጥ በማለት ቈራጦች ለመሆናቸው ምስክራቸው እኔ ነኝና። ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት መላልሰው ማለዱን። እነርሱ አስቀድመው በፈቃዳቸው፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔርም፥ ለእኛም አሳልፈው ሰጥተዋልና እኛ እንደ አሰብነው አይደለም፤ ይህንም የቸርነት ሥራ እንደ ጀመረ ይፈጽምላችሁ ዘንድ ቲቶን ማለድነው። በሁሉ ነገር በእምነትና በቃል፥ በዕውቀትም፥ በትጋትም በእናንተ ዘንድ በሆነው ሁሉ እኛን በመውደዳችሁ ፍጹማን እንደ ሆናችሁ፥ እንዲሁም ደግሞ ይህቺን ስጦታ አብዙ። በግድ የምላችሁ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ለዚህ ሥራ የሚተጉለት አሉና የፍቅራችሁን እውነተኛነት አሁን መርምሬ ተረዳሁ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸርነቱን ታውቃላችሁ፤ በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጸጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ባለጸጋ ሲሆን፥ ስለ እናንተ ራሱን ድሃ አደረገ።
2 ቆሮንቶስ 8:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን። የደረሰባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም ደስታቸው ግን የላቀ ነበር፤ ድኽነታቸው ብርቱ ቢሆንም ልግስናቸው ግን የበዛ ነበር። እንደ ዐቅማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከዐቅማቸው በላይ በፈቃዳቸው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁ። እነርሱም ቅዱሳንን ለመርዳት በሚደረገው አገልግሎት ለመሳተፍ ዕድል ያገኙ ዘንድ አጥብቀው ይለምኑን ነበር። እኛ ከጠበቅነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ። ስለዚህ ቲቶ፣ በእናንተ መካከል ቀደም ሲል የጀመረውን የልግስና ሥራ ከፍጻሜ እንዲያደርስ ለምነነው ነበር። እናንተም በሁሉ ነገር ይኸውም በእምነት፣ በቃል፣ በዕውቀት፣ በፍጹም ትጋትና ለእኛም ባላችሁ ፍቅር ልቃችሁ እንደ ተገኛችሁ፣ በዚህም የቸርነት ሥራ ልቃችሁ እንድትገኙ ዐደራ እንላችኋለን። ይህን የምለው ትእዛዝ ለመስጠት ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን ሌሎች ከሚያሳዩት ትጋት አንጻር የፍቅራችሁን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ነው። የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ።
2 ቆሮንቶስ 8:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥ አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም። ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ እንደ ጀመረ እንዲሁ ደግሞ ይህን ቸር ሥራ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ሊፈጽም ለመንን። ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ። ትእዛዝ እንደምሰጥ አልልም፥ ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ፤ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ።
2 ቆሮንቶስ 8:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! በመቄዶንያ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንድታውቁት እንፈልጋለን፤ በብዙ መከራ እየተፈተኑም ቢሆን ደስታቸው እጥፍ ድርብ ነበር፤ የድህነታቸው መጠን ቢበዛም ልግስናቸው የበዛ ነበር። እንደ ዐቅማቸው መጠን፥ ዐቅማቸውም የሚያልፍ እንኳን፥ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁ። ለቅዱሳን በሚደረገው አገልግሎት እነርሱም ተሳታፊ የመሆንን ጸጋ እንዲያገኙ እኛን አጥብቀው ይለምኑ ነበር፤ አስቀድመው ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፥ ከዚያም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለእኛም ሰጡ፥ እንጂ እኛ አስበንበት ያደረግነው አይደለም። ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ በእናንተ መካከል የጀመረውን ይህንን የቸርነት ከፍጻሜ እንዲያደርሰው ለምነነው ነበር። ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነት፥ በቃል፥ በእውቀት፥ በትጋት፥ እንዲሁም ለእኛ በፍቅራችሁ ልቃችሁ እንደተገኛችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ልቃችሁ ተገኙ። ይህንን የምለው ትእዛዝ እንደምሰጥ ሆኜ አይደለም፤ ነገር ግን ሌሎች ከሚያሳዩት ትጋት አንጻር የፍቅራችሁን እውነተኛነት ለመመርመር ነው። የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ ታውቃላችሁ፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ።