የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 9

9
የንግሥተ ሳባ ጒብኝት በኢየሩሳሌም
(1ነገ. 10፥1-13)
1ንግሥተ ሳባ ስለ ሰሎሞን የሚነገረውን አስደናቂ ጥበብ ሁሉ ሰማች፤ ስለዚህ አስቸጋሪ በሆኑ የእንቆቅልሽ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች፤ ወደ ኢየሩሳሌም ስትመጣም ብዙ የክብር አጃቢዎችን አስከትላ ሽቶ፥ የከበሩ ዕንቆችና እጅግ የበዛ ወርቅ በግመሎች አስጭና ነበር፤ ከሰሎሞንም ጋር በተገናኘች ጊዜ በሐሳብዋ የነበረውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት፤ 2እርሱም ላቀረበችለት ጥያቄ ሁሉ መልስ ሰጠ፤ ሊተረጒምላት የተሳነውና ከእርሱ የተሰወረ ምንም ዐይነት እንቆቅልሽ አልነበረም። 3ንግሥተ ሳባም ጥበብ የተሞላበትን የሰሎሞንን አነጋገር አዳመጠች፤ እርሱ ያሠራውንም ቤተ መንግሥት አየች፤ 4በሰሎሞን ገበታ ላይ የሚቀርበውን የምግብ ዐይነት፥ የመኳንንቱ አቀማመጥ፥ የቤተ መንግሥቱን ሠራተኞች የሥራ አደረጃጀት፥ የመጠጥ አሳላፊዎቹ የደንብ ልብስ ዐይነት፥ በግብዣ ጊዜ የሚያገለግሉትን አሳላፊዎችና በቤተ መቅደስም የሚያቀርባቸውን መሥዋዕቶች ሁሉ ተመለከተች፤ በዚህም ሁሉ የተሰማት አድናቆት ከጠበቀችው በላይ ነበር።
5ንጉሥ ሰሎሞንንም እንዲህ አለችው “ስለ አንተ ሥራና ስለ ጥበብህ ታላቅነት በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው! 6ይሁን እንጂ እዚህ መጥቼ ሁሉን ነገር በዐይኔ እስካየሁ ድረስ የተነገረኝን ሁሉ አላመንኩም ነበር፤ ታዲያ በጆሮዬ የሰማሁት በዐይኔ ያየሁትን እኩሌታ እንኳ አልሆነም፤ በእርግጥም ጥበብህ ከተነገረኝ በጣም ይበልጣል፤ 7ዘወትር በአንተ ፊት በመገኘት ጥበብ የተሞላበት ንግግርህን የሚሰሙ ባለሟሎችና አገልጋዮችህ እንዴት የታደሉ ናቸው! 8ንጉሥ ሆነህ በእርሱ ስም ትገዛ ዘንድ አንተን መርጦ የእስራኤል ንጉሥ ለማድረግ መልካም ፈቃዱ ስለ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን! በፍቅሩም እስራኤል ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር ስለ ፈለገ ሕግና ፍትሕ ጸንቶ እንዲኖር ታደርግ ዘንድ አንተን መርጦ ንጉሥ አድርጎሃል።”
9ንግሥተ ሳባ ያመጣችውን ከአራት ሺህ ኪሎ የሚበልጥ ወርቅ፥ እጅግ ብዙ ሽቶና ዕንቊ ገጸ በረከት አድርጋ ለሰሎሞን ሰጠችው፤ እርስዋ ለሰሎሞን የሰጠችው የሽቶ ዐይነት፥ ከዚያ በፊት ከቶ ታይቶ የማይታወቅ ነው። #ማቴ. 12፥42፤ ሉቃ. 11፥31።
10ከኦፊር ወርቅ ያመጡ የንጉሥ ኪራምና የንጉሥ ሰሎሞን ሰዎች ከዚያው ከኦፊር የሰንደል እንጨትና ዕንቊ ለሰሎሞን አምጥተውለት ነበር፤ 11ሰሎሞንም የሰንደሉን እንጨት የቤተ መቅደሱንና የቤተ መንግሥቱን ደረጃዎች እንዲሁም የመዘምራኑን መሰንቆና በገና አሠራበት፤ እነዚህን የዜማ መሣሪያዎች የመሰለ ከዚያ በፊት በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም።
12ንጉሥ ሰሎሞን እርስዋ ካመጣችው ስጦታ በላይ የሳባ ንግሥት የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚህ በኋላ ንግሥተ ሳባ ከክብር አጃቢዎችዋ ጋር ወደ አገርዋ ተመልሳ ሄደች።
የንጉሥ ሰሎሞን ሀብት ብዛት
(1ነገ. 10፥14-25)
13ንጉሥ ሰሎሞን በየዓመቱ ኻያ ሦስት ሺህ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ወርቅ ያገኝ ነበር፤ 14ይህም ነጋዴዎች ከሚከፍሉት ቀረጥ፥ እንዲሁም ከዐረብ ነገሥታትና ከእስራኤል ክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ከሚገባለት ግብር ሌላ ተጨማሪ ነበር።
15ንጉሥ ሰሎሞን እያንዳንዳቸው ሰባት ኪሎ በሚያኽል ንጹሕ ወርቅ የተለበጡ ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻዎችንና 16እያንዳንዳቸው ሦስት ኪሎ በሚያኽል ንጹሕ ወርቅ የተለበጡ ሦስት መቶ አነስተኛ ጋሻዎችን አሠርቶ ነበር፤ እነዚህንም ሁሉ ጋሻዎች “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ አኖራቸው።
17እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ከዝሆን ጥርስ አንድ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው፤ 18-19ዙፋኑም ከታች ወደ ላይ መወጣጫ የሆኑ ስድስት ደረጃዎች ነበሩት፤ በእያንዳንዱም ደረጃ ጫፍ በግራና በቀኝ አንዳንድ የአንበሳ ምስል ሲኖር በድምሩ የተቀረጹት የአንበሳ ምስሎች ዐሥራ ሁለት ነበሩ፤ ከዙፋኑ ጋር ተያይዞ ከወርቅ የተሠራ የእግር መረገጫም ነበረው፤ በሁለቱ የክንድ መደገፊያ ጫፎችም ላይ አንዳንድ የአንበሳ ምስል ነበር፤ በሌላ በየትኛውም አገር መንግሥት ይህን የመሰለ ዙፋን ከቶ አልነበረም።
20ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዋንጫዎችና “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ የሚገኙት ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ከመብዛቱ የተነሣ ዋጋ እንዳለው ሆኖ አይቈጠርም ነበር። 21ሰሎሞንም በኪራም አገልጋዮች አማካይነት ወደ ተርሴስ የሚጓዙ መርከቦች ነበሩት፤ እነርሱም በየሦስት ዓመቱ ወርቅን፥ ብርን፥ የዝሆን ጥርስን፥ ጦጣዎችንና ዝንጀሮዎችን ያመጡለት ነበር።
22ንጉሥ ሰሎሞን በዓለም ከሚገኝ ከማንኛውም ንጉሥ ይበልጥ ሀብታምና ጥበበኛ ነበር፤ 23በመላው ዓለም የሚገኙ ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ የሞላበትን ንግግር ይሰሙ ዘንድ ከሰሎሞን ጋር መገናኘት ይፈልጉ ነበር። 24ወደ እርሱም የሚመጡት ሁሉ የብርና የወርቅ፥ የልብስ፥ የጦር መሣሪያዎች፥ የሽቶ፥ የፈረሶችና የበቅሎዎች ስጦታዎችን ያመጡለት ነበር፤ ይህም በየዓመቱ የሚደረግ ነበር።
25ንጉሥ ሰሎሞን ለሠረገሎቹና ለፈረሶቹ አራት ሺህ ጋጣዎች፥ እንዲሁም ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ ከእነርሱም ከፊሉን በኢየሩሳሌም፥ የቀሩትም ደግሞ በሌሎች ልዩ ልዩ ከተሞች ተመድበው እንዲኖሩ አደረገ፤ #1ነገ. 4፥26። 26ሰሎሞን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ግዛት ዳርቻ ድረስ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ያስገብር ነበር፤ #ዘፍ. 15፥18፤ 1ነገ. 4፥21። 27በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኢየሩሳሌም ብር እንደ ድንጋይ፥ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ብዛት በይሁዳ ኰረብቶች ግርጌ በየትኛውም ስፍራ እንደሚበቅል ሾላ ይቈጠር ነበር። 28ሰሎሞን ከግብጽና ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶችን ያስመጣ ነበር። #ዘዳ. 17፥16።
የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ታሪክ ባጭሩ
(1ነገ. 11፥41-43)
29ሌላው የሰሎሞን ታሪክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በነቢዩ ናታን ታሪክ፥ የሴሎ ተወላጅ በሆነው በነቢዩ አኪያ ትንቢትና ስለ እስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ጭምር በሚናገረው በነቢዩ ዒዶ ራእይ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 30ሰሎሞን መኖሪያውን በኢየሩሳሌም አድርጎ በመላው እስራኤል ላይ አርባ ዓመት ነገሠ፤ 31ከዚያም በኋላ ሞተ፤ በዳዊት ከተማም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሮብዓም ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ