ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35
35
ኢዮስያስ የፋሲካን በዓል ማክበሩ
(2ነገ. 23፥21-23)
1ንጉሥ ኢዮስያስ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ክብር የፋሲካን በዓል አከበረ፤ የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ሕዝቡ የፋሲካን በግ ዐረደ፤ 2ካህናት የሚያከናውኑትን ተግባር መድቦ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ አበረታታቸው፤ 3እንዲሁም ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለለዩ፥ የመላው እስራኤል መምህራን ለሆኑ ሌዋውያን እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጠ፦ “የተቀደሰውን የቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ልጅ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ አኑሩት፤ ከእንግዲህ ወዲህ እናንተ አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን ማገልገል እንጂ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት በትከሻችሁ ተሸክማችሁ ከስፍራ ወደ ስፍራ መውሰድ የለባችሁም። 4ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ንጉሥ ሰሎሞን በሰጡአችሁ መመሪያ መሠረት በየጐሣችሁ በመመደብ በቤተ መቅደስ አገልግሎት ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ #2ዜ.መ. 8፥14። 5እናንተ ሌዋውያን፥ እያንዳንዱን የእስራኤል ሕዝብ ቤተሰብ ለመርዳት እንድትችሉ እየተከፋፈላችሁ በተቀደሰው ስፍራ በቦታ በቦታቸው ራሳችሁን አደራጁ። 6ወገኖቻችሁ የሆኑ እስራኤላውያን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ ይከተሉ ዘንድ ራሳችሁን አንጽታችሁ የፋሲካን በግ ዕረዱ።”
7ንጉሥ ኢዮስያስ በዚያው በፋሲካ በዓል የተገኙ ሰዎች መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡአቸውን የራሱ ሀብት ከሆኑ የቀንድ ከብቶች፥ እንዲሁም የበግና የፍየል መንጋ፥ ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶችንና ሦስት ሺህ ወይፈኖችን ሰጠ፤ 8የንጉሡ ባለሟሎች የሆኑ ባለሥልጣኖችም መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡ እንስሶችን በገዛ ፈቃዳቸው ለምእመናን፥ ለካህናትና ለሌዋውያን ሰጡ፤ የቤተ መቅደሱ አለቆች የሆኑት ሊቃነ ካህናቱ ሒልቂያ፥ ዘካርያስና ይሒኤልም የፋሲካ መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ የበግና የፍየል ጠቦቶችንና ሦስት መቶ በሬዎችን ለካህናት ሰጡ፤ 9የሌዋውያን አለቆች ኮናንያና ወንድሞቹ የሆኑ ሸማዕያና ነታንኤል እንዲሁም ሐሻብያ፥ ይዒኤልና ዮዛባድ ሌዋውያኑ ለፋሲካ በዓል መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡአቸውን አምስት ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶችን እንዲሁም አምስት መቶ በሬዎችን ሰጡ።
10ለፋሲካው በዓል የሚሆነው ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ፥ ካህናቱ በስፍራቸውና ሌዋውያኑም በየክፍላቸው በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ቦታ ቦታቸውን ያዙ፤ 11ለፋሲካውም በዓል የታረዱትን የበግና የፍየል ጠቦቶች ሌዋውያኑ ቆዳቸውን ገፈፉአቸው፤ ካህናቱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩ፤ 12ለሚቃጠል መሥዋዕት የቀረቡትን እንስሶች በየቤተሰቡ ለተመደበው ሕዝብ አከፋፈሉ፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት በኦሪት ሕግ በተሰጠው መመሪያ መሠረት መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ነው፤ እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ፤ 13ሌዋውያኑም በሕጉ መሠረት የፋሲካውን መሥዋዕት በእሳት ጠበሱት፤ የተቀደሰውንም ቊርባን በምንቸት፥ በሰታቴና በድስት ቀቅለው ሥጋውን በፍጥነት ለሕዝቡ አከፋፈሉ፤ #ዘፀ. 12፥8-9። 14ከዚህም በኋላ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ካህናት የፋሲካን መሥዋዕት አዘጋጁ፤ ይህንንም ያደረጉት ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን በሙሉ ለማቃጠል እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ስለ ነበር ነው፤ 15ከዚህ በታች ስማቸው የተመለከተው የሌዋዊው የአሳፍ ጐሣ የሆኑ መዘምራንም ንጉሥ ዳዊት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፥ በተመደበላቸው ስፍራ ነበሩ፤ እነርሱም አሳፍ፥ ሄማንና የንጉሡ ነቢይ ይዱታን ናቸው፤ ሌሎች ሌዋውያን የፋሲካውን መሥዋዕት ያዘጋጁላቸው ስለ ነበር፥ የቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎች ስፍራቸውን አይተዉም ነበር፤ #1ዜ.መ. 25፥1። 16በዚህም ዐይነት ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት፥ የፋሲካ በዓል አከባበርና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ የማቅረቡ ሥራ ሁሉ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በዚያ ቀን ተከናወነ። 17በዚያ የነበሩ እስራኤላውያን ሁሉ የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ እንዲሁም ለሰባት ቀን የቂጣን በዓል አከበሩ፤ #ዘፀ. 12፥1-20። 18ከነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ጀምሮ የፋሲካ በዓል ይህን በመሰለ ሁኔታ ከቶ ተከብሮ አያውቅም፤ ንጉሥ ኢዮስያስ፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ የይሁዳ፥ የእስራኤልና የኢየሩሳሌም ሕዝብ የፋሲካን በዓል አሁን ባከበሩት ዐይነት ከዚህ በፊት ከነበሩት ነገሥታት መካከል፥ አንዱ እንኳ አክብሮ አያውቅም፤ 19ይህም በዓል የተከበረው፥ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ነበር።
የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(2ነገ. 23፥28-30)
20ንጉሥ ኢዮስያስ ለቤተ መቅደሱ ይህን ሁሉ ካደራጀ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው ካርከሚሽ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ አደጋ ለመጣል ሠራዊቱን አሰልፎ መጣ፤ ኢዮስያስም ሊቋቋመው ተነሣ፤ 21ኒካዑ ግን ለኢዮስያስ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ እኔንና አንተን የሚያጣላን ምንም ነገር የለም፤ እኔ የመጣሁት ጠላቶቼን ለመውጋት እንጂ፥ አንተን ለመውጋት አይደለም፤ ጠላቶቼንም በፍጥነት እንድወጋ እግዚአብሔር አዞኛል፤ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ስለ ሆነ፥ ባትቃወመኝ ይሻልሃል፤ እምቢ ብትል ግን እግዚአብሔር ያጠፋሃል” የሚል መልእክት ላከበት፤ 22ኢዮስያስ ግን ጦርነት ለመግጠም ቊርጥ ውሳኔ አደረገ፤ እግዚአብሔር በንጉሥ ኒካዑ አማካይነት የተናገረውንም ሊሰማ አልፈለገም፤ ልብሰ መንግሥቱን ለውጦ ሌላ ሰው በመምሰል በመጊዶ ወደሚገኘው ሜዳ ሊዋጋ ሄደ።
23ጦርነቱም በመፋፋም ላይ ሳለ፥ ንጉሥ ኢዮስያስ ከግብጽ ወታደሮች በተወረወረ ቀስት ተወጋ፤ እርሱም አገልጋዮቹን፥ “ክፉኛ ቈስያለሁና ከጦር ሜዳው አውጡኝ!” ሲል አዘዛቸው፤ 24እነርሱም ከሠረገላው አውጥተው እዚያ በነበረው በሌላ ሠረገላ ውስጥ በማስቀመጥ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዚያም ሞተ፤ በነገሥታትም መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች ሁሉ አለቀሱለት።
25ነቢዩ ኤርምያስም ለንጉሥ ኢዮስያስ የለቅሶ ሙሾ አወጣለት፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች አልቃሾች ኢዮስያስን በማስታወስ፥ በሚያለቅሱበት ጊዜ በዚሁ በነቢዩ ኤርምያስ የለቅሶ ሙሾ ማልቀስ በእስራኤል አገር የተለመደ ሆነ፤ ይህም የለቅሶ ሙሾ የእስራኤልን የለቅሶ ሰቆቃ በያዘ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።
26ኢዮስያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር የነበረው ታላቅ ፍቅር፥ ለእግዚአብሔር ሕግ የነበረው ታዛዥነት፥ 27ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለው የእርሱ ታሪክ ጭምር በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997