ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 29
29
የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ
(2ነገ. 18፥1-3)
1ሕዝቅያስ ዕድሜው ኻያ አምስት ዓመት ሲሆነው ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኻያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፤ እናቱ አቢያ ተብላ የምትጠራ የዘካርያስ ልጅ ነበረች። 2ሕዝቅያስ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም ምሳሌነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ።
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደገና የመንጻት ተግባር
3ሕዝቅያስ በነገሠበት ዓመት በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በር ሁሉ እንደገና ከፍቶ አደሰ፤ 4ካህናትንና ሌዋውያንን በስተ ምሥራቅ በኩል በሚገኘው በቤተ መቅደሱ አደባባይ ሰበሰባቸው፤ 5እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሌዋውያን! ራሳችሁን መቀደስና የቀድሞ አባቶቻችሁን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቀደስ ማንጻት አለባችሁ፤ ቤተ መቅደሱን የሚያረክስ ነገር ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ማስወገድ ይኖርባችኋል። 6የቀድሞ አባቶቻችን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት አጓድለዋል፤ እርሱንም በመተው የእርሱ መኖሪያ ከሆነው ስፍራ ፊታቸውን አዞሩ፤ 7የቤተ መቅደሱን በር ሁሉ ዘጉ፤ መብራቶቹንም አጠፉ፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ዕጣንን ማጠን ወይም የሚቃጠል መሥዋዕትን ማቅረብ ተዉ፤ 8በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ፤ እናንተም እንደምታዩት በእነርሱ ላይ ፍርሀትንና ድንጋጤን አምጥቶባቸዋል፤ መዘባበቻም አድርጎአቸዋል። 9ስለዚህ አባቶቻችን በጦርነት ተገድለዋል፤ ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ሁሉ እስረኞች ሆነው ተወስደዋል።
10“ከእንግዲህ ወዲህ የእግዚአብሔር ቊጣ ከእኛ እንዲርቅ እነሆ እኔ አሁን ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ወስኛለሁ፤ 11ልጆቼ ሆይ! በፊቱ ቆማችሁ እንድታገለግሉትና የእርሱ አገልጋዮች እንድትሆኑ፥ መሥዋዕትንም እንድታቀርቡ እግዚአብሔር የመረጣችሁ ስለ ሆነ እንግዲህ ቸልተኞች አትሁኑ።”
12-14ሥራውን እንዲቀጥሉ የተደረጉት ስማቸው ከዚህ በታች የተዘረዘረው ሌዋውያን እነዚህ ነበሩ፦
ከቀዓት ጐሣ፦ የዐማሣይ ልጅ ማሐትና የዐዛርያስ ልጅ ኢዩኤል፤
ከመራሪ ጐሣ፦ የዓብዲ ልጅ ቂሽና የይሀልኤል ልጅ ዐዛርያስ፤
ከጌርሾን ጐሣ፦ የዚማ ልጅ ዮአሕና የዮአሕ ልጅ ዔዴን፤
ከኤሊጻፋን ጐሣ፦ ሺምሪና ይዒኤል፤
ከአሳፍ ጐሣ፦ ዘካርያስና ማታንያ፤
ከሄማን ጐሣ፦ ይሒኤልና ሺምዒ፤
ከይዱቱን ጐሣ፦ ሸማዕያና ዑዚኤል።
15እነዚህም ሰዎች ሌዋውያን ወገኖቻቸውን ሰብስበው ሁሉም በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት ራሳቸውን አነጹ፤ ከዚህም በኋላ ንጉሡ እንዳዘዛቸው ሌዋውያኑ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት ቤተ መቅደሱን አነጹ፤ 16ካህናቱም ቤተ መቅደሱን ለማንጻት ወደ ውስጡ ገቡ፤ ያልነጻውንም ነገር ሁሉ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ አወጡት፤ ሌዋውያኑም ከዚያ አንሥተው ከከተማ ውጪ በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ጣሉት።
17የማንጻቱ ሥራ በመጀመሪያው ወር መባቻ ቀን ተጀምሮ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ የሚያስገባው ክፍል ጭምር ሙሉ በሙሉ ተፈጸመ፤ ከዚህ በኋላም ቤተ መቅደሱን ለአምልኮ ሥነ ሥርዓት ለማዘጋጀት በተከታዮቹ ስምንት ቀኖች ማለትም ወሩ በገባ እስከ ዐሥራ ስድስተኛው ቀን ድረስ ሠሩ።
ቤተ መቅደሱ እንደገና ለእግዚአብሔር የተለየ መሆኑ
18ሌዋውያኑ ስለ ተከናወነው ሥራ ለንጉሥ ሕዝቅያስ የሚከተለውን መግለጫ አቀረቡ፦ “የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ፥ የተቀደሰው ኅብስት የሚቀመጥበትን ገበታና ከእነርሱም ጋር የተያያዙትን ሌሎች ዕቃዎች ጭምር ቤተ መቅደሱን በሙሉ አንጽተናል፤ 19እንዲሁም ንጉሥ አካዝ ለእግዚአብሔር ታማኝ ባልነበረባቸው ዓመቶች ወስዶት የነበረውን ዕቃ ሁሉ መልሰን በማምጣት ለእግዚአብሔር የተለዩ እንዲሆኑ አድርገናል፤ እነዚህም ዕቃዎች በሙሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ፊት ለፊት ባለው ስፍራ ይገኛሉ።”
20በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማይቱን ባለሥልጣኖች ሰብስቦ እነርሱን በማስከተል ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደ፤ 21እነርሱም ለንጉሣዊው ቤተሰብና ለይሁዳ ሕዝብ የኃጢአት ስርየት፥ እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ መንጻት መሥዋዕት ሆነው ለእግዚአብሔር ይቀርቡ ዘንድ ሰባት ኰርማዎችን፥ ሰባት የበግ አውራዎችን፥ ሰባት የበግ ጠቦቶችንና ሰባት ፍየሎችን አመጡ፤ ንጉሡም የአሮን ዘሮች የሆኑትን ካህናት እንስሶቹን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ አዘዛቸው፤ 22ካህናቱም በመጀመሪያ ኰርማዎቹን፥ ቀጥሎም በጎቹን፥ በመጨረሻም የበግ ጠቦቶቹን ዐርደው የእያንዳንዱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ 23ከዚህ በኋላም ፍየሎቹን ወደ ንጉሡና ወደተሰበሰቡት ሰዎች አቀረቡአቸው፤ ንጉሡና ሰዎቹም እጃቸውን ጫኑባቸው። 24ንጉሡ ስለ መላው የእስራኤል ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕትና ለኃጢአት ስርየት የሚሆን መሥዋዕት እንዲቀርብ አዞ ስለ ነበር፥ ካህናቱ በትእዛዙ መሠረት ፍየሎቹን ዐርደው ደማቸውን መሥዋዕት በማድረግ በመሠዊያው ላይ አፈሰሱ።
25ንጉሥ ሕዝቅያስ እግዚአብሔር በነቢዩ ጋድና በነቢዩ ናታን አማካይነት ለንጉሥ ዳዊት የሰጠውንና ዳዊትም ተግባራዊ ያደረገውን ትእዛዝ በመከተል በበገና፥ በጸናጽልና በመሰንቆ የሠለጠኑ ሌዋውያንን በቤተ መቅደሱ ውስጥ መደበ፤ 26ሌዋውያን እነዚህን ዳዊት ይጠቀምባቸው የነበሩትን የዜማ መሣሪያዎች ይዘው፥ ካህናቱም እምቢልታ ይዘው በዚያው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቆሙ፤ 27ንጉሥ ሕዝቅያስ የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ያሳርጉ ዘንድ አዘዘ፤ መሥዋዕቱንም ማሳረግ ሲጀምሩ ሕዝቡ የምስጋና መዝሙር አቀረበ፤ መዘምራኑም እምቢልታ መንፋትና በዳዊት የዜማ መሣሪያዎች በመታጀብ ማዜም ጀመሩ፤ 28በዚያ የነበረ ሕዝብም ሁሉ በኅብረት ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ መሥዋዕቱም ሁሉ ፈጽሞ እስከሚቃጠል ድረስ እምቢልተኞቹ እምቢልታቸውን ይነፉ ነበር። 29መሥዋዕቱን የማቅረብ ሥራ በተፈጸመ ጊዜ ንጉሥ ሕዝቅያስና በዚያ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተንበርክከው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። 30ንጉሡና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ በዳዊትና በነቢዩ አሳፍ የተደረሱትን የምስጋና መዝሙሮች ለእግዚአብሔር ክብር እንዲዘምሩ ሌዋውያንን አዘዙ፤ ስለዚህ ሁሉም ተንበርክከው በመስገድ ላይ ሳሉ በታላቅ ደስታ ይዘምሩ ነበር።
31ንጉሥ ሕዝቅያስም ሕዝቡን “አሁን ራሳችሁን ለእግዚአብሔር የለያችሁ ስለ ሆነ ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ መሥዋዕታችሁን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ!” አላቸው፤ እነርሱም ንጉሡ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አንዳዶቹም በገዛ ፈቃዳቸው ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶችን አመጡ፤ 32በዚህ ዐይነት ሕዝቡ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ ያመጡአቸው እንስሶች ብዛት ሰባ ኰርማዎች፥ አንድ መቶ የበግ አውራዎችና ሁለት መቶ የበግ ጠቦቶች ነበሩ። 33በተጨማሪ ለአንድነት መሥዋዕት የተለዩ እንስሶች ብዛት ስድስት መቶ በሬዎችና ሦስት ሺህ አውራ በጎች ነበሩ፤ 34ይህን ሁሉ እንስሳ ዐርደው ቆዳውን ለመግፈፍ በቂ ካህናት ስላልነበሩ ሥራው እስኪጠናቀቅና የነጹ ካህናት እስከሚገኙ ድረስ ሌዋውያን ይረዱአቸው ነበር፤ በመንጻት ረገድ ከካህናት ይልቅ ሌዋውያን ዘወትር ዝግጁዎች ነበሩ። 35ብዙ ከሆነው የሚቃጠል መሥዋዕት ለደኅንነት መሥዋዕት የሚቀርበው ስብ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር የሚቀርበው የመጠጥ ቊርባን ነበር።
በዚህ ሁኔታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚደረገው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት እንደገና ተጀመረ፤ 36ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ይህን ሁሉ በተፋጠነ አኳኋን ለማከናወን እግዚአብሔር ስለ ረዳቸው እጅግ ተደሰቱ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 29: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997