ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26:14-21

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26:14-21 አማ05

ዖዝያም ለመላው ሠራዊቱ ጋሻና ጦር፥ የራስ ቊርና የደረት ጥሩርን፥ ቀስትና ፍላጻን፥ ወንጭፍና የሚወነጨፉ ድንጋዮችን አዘጋጅቶለት ነበር፤ ንጉሥ ዖዝያ በኢየሩሳሌም በእጅ ሥራ ጥበብ የሠለጠኑ ሰዎች ከመጠበቂያ ግንቦችና ከከተማይቱ ቅጽር ማእዘኖች ላይ ፍላጻዎችንና ታላላቅ ድንጋዮችን የሚያስፈነጥሩ መሣሪያዎችን እንዲሠሩ አደረገ፤ እግዚአብሔር ስለ ረዳውም እጅግ በረታ፤ እጅግም ገናና ሆነ፤ ዝናውም በሁሉ ስፍራ ተሰማ። ንጉሥ ዖዝያ መንግሥቱን ባጠናከረ ጊዜ ዕብሪተኛ ሆነ፤ ይህም ዕብሪተኛነቱ ወደ ውድቀት አደረሰው፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ ቤተ መቅደስ በድፍረት በመግባቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ በዚህ ጊዜ ካህኑ ዐዛርያስና ከእርሱም ጋር ልበ ሙሉና ቈራጥ የሆኑ ሰማኒያ ካህናት ድርጊቱን ለመቃወም ንጉሡን ተከትለው ወደ ቤተ መቅደሱ ገቡ። እንዲህም አሉት፦ “ዖዝያ ሆይ! አንተ ለእግዚአብሔር ዕጣን ታጥን ዘንድ አይገባህም፤ ይህን ለማድረግ የተመደቡት ለእግዚአብሔር የተለዩት የአሮን ልጆች የሆኑት ካህናት ብቻ ናቸው፤ ስለዚህ ከዚህ ከተቀደሰው ስፍራ ውጣ፥ እግዚአብሔር አምላክን አሳዝነሃል፤ ይህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን የሚያስገኝልህ ድርጊት አይደለም።” ዕጣን ለማጠን ዝግጁ ሆኖ ጥናውን በእጁ እንደ ያዘ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው አጠገብ ቆሞ የነበረው ዖዝያም በካህናቱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ወዲያውኑ በግንባሩ ላይ የቆዳ በሽታ ታየ። ዐዛርያስና ሌሎቹም ካህናት በታላቅ ድንጋጤ የንጉሡን ግንባር ትኲር ብለው ተመለከቱ፤ ከቤተ መቅደስም እንዲወጣ አስገደዱት፤ ዖዝያም እግዚአብሔር እንደ ቀጣው ዐውቆ ለመውጣት ተጣደፈ። ንጉሥ ዖዝያ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የቆዳው በሽታ አለቀቀውም፤ ይህም በመሆኑ በተለየ ቤት ኖረ፤ ከእግዚአብሔርም ቤት እንዲገለል ተደረገ፤ ልጁ ኢዮአታም የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በመሆን የአገሪቱን ሕዝብ ያስተዳድር ነበር።