ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26
26
የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያ
(2ነገ. 14፥21-22፤ 15፥1-7)
1መላው የይሁዳ ሕዝብ ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን የአሜስያስን ልጅ ዖዝያን በአባቱ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ መረጡት። 2(ዖዝያ ኤላትን መልሶ በመያዝ ከተማይቱን እንደገና የሠራው ከአባቱ ከአሜስያስ ሞት በኋላ ነው።)
3ዖዝያ በዐሥራ ስድስት ዓመቱ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኀምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። 4ዖዝያ የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ፤ 5መንፈሳዊ አማካሪው ዘካርያስ በሕይወት እስከ ነበረበት ዘመን ድረስ ዖዝያ እግዚአብሔርን በታማኝነት ያገለግል ነበር፤ እግዚአብሔርም ባረከው።
6ዖዝያ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጥሎ የጋትን፥ የያብኔንና የአሽዶድን ከተማዎች ቅጽሮችን አፈራረሰ፤ በአሽዶድ አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛት ውስጥ የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። 7ፍልስጥኤማውያንን፥ በጒርባዓል ይኖሩ የነበሩትን ዐረቦችና መዑናውያንን ድል እንዲያደርግ እግዚአብሔር ረዳው። 8ዐሞናውያንም ለዖዝያ ገበሩለት፤ እጅግ እየገነነ በመሄዱ ዝናው እስከ ግብጽ ድረስ ተሰማ።
9ዖዝያ በማእዘን ቅጽር በር፥ በሸለቆ ቅጽር በርና በቅጽሩም መጠምዘዣ ላይ መቈጣጠሪያ ግንቦችን በመሥራት የኢየሩሳሌምን ምሽጎች አጠናከረ፤ 10በምዕራባዊ ኰረብቶች ግርጌና በሜዳዎች ላይ ብዙ የቀንድ ከብቶች ስለ ነበሩትም በገጠር የተመሸጉ መጠበቂያ ግንቦችን ሠራ፤ ብዙ ጒድጓዶችንም ማሰ፤ ግብርና ይወድ ስለ ነበረ በኰረብታማ አገሮችና በለሙ ቦታ የወይን ተክል ተካዮችና ገበሬዎች ነበሩት።
11ዖዝያ ለጦርነት ዝግጁ የሆነ እጅግ የበዛ ሠራዊት ነበረው፤ የሠራዊቱም አባላት ስም ዝርዝር የንጉሡ ጸሐፊዎች በሆኑት በይዒኤልና በማዕሤያ ይመዘገብ ነበር፤ የእነርሱም የበላይ ተቈጣጣሪ የቤተ መንግሥቱ ሠራተኞች አባል የሆነው ሐናንያ ነበር። 12ሠራዊቱም የሚመራው በሁለት ሺህ ስድስት መቶ የጐሣ መሪዎች ነበር፤ 13በእነርሱም ሥልጣን ሥር የንጉሡን ጠላቶች ለመመከት በቂ ችሎታ ያላቸው ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ጀግኖች ወታደሮች ነበሩ፤ 14ዖዝያም ለመላው ሠራዊቱ ጋሻና ጦር፥ የራስ ቊርና የደረት ጥሩርን፥ ቀስትና ፍላጻን፥ ወንጭፍና የሚወነጨፉ ድንጋዮችን አዘጋጅቶለት ነበር፤ 15ንጉሥ ዖዝያ በኢየሩሳሌም በእጅ ሥራ ጥበብ የሠለጠኑ ሰዎች ከመጠበቂያ ግንቦችና ከከተማይቱ ቅጽር ማእዘኖች ላይ ፍላጻዎችንና ታላላቅ ድንጋዮችን የሚያስፈነጥሩ መሣሪያዎችን እንዲሠሩ አደረገ፤ እግዚአብሔር ስለ ረዳውም እጅግ በረታ፤ እጅግም ገናና ሆነ፤ ዝናውም በሁሉ ስፍራ ተሰማ።
ዖዝያ በዕብሪተኛነቱ ተቀጣ
16ንጉሥ ዖዝያ መንግሥቱን ባጠናከረ ጊዜ ዕብሪተኛ ሆነ፤ ይህም ዕብሪተኛነቱ ወደ ውድቀት አደረሰው፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ ቤተ መቅደስ በድፍረት በመግባቱ እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ 17በዚህ ጊዜ ካህኑ ዐዛርያስና ከእርሱም ጋር ልበ ሙሉና ቈራጥ የሆኑ ሰማኒያ ካህናት ድርጊቱን ለመቃወም ንጉሡን ተከትለው ወደ ቤተ መቅደሱ ገቡ። 18እንዲህም አሉት፦ “ዖዝያ ሆይ! አንተ ለእግዚአብሔር ዕጣን ታጥን ዘንድ አይገባህም፤ ይህን ለማድረግ የተመደቡት ለእግዚአብሔር የተለዩት የአሮን ልጆች የሆኑት ካህናት ብቻ ናቸው፤ ስለዚህ ከዚህ ከተቀደሰው ስፍራ ውጣ፥ እግዚአብሔር አምላክን አሳዝነሃል፤ ይህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን የሚያስገኝልህ ድርጊት አይደለም።” #ዘፀ. 30፥7-8፤ ዘኍ. 3፥10።
19ዕጣን ለማጠን ዝግጁ ሆኖ ጥናውን በእጁ እንደ ያዘ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው አጠገብ ቆሞ የነበረው ዖዝያም በካህናቱ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ወዲያውኑ በግንባሩ ላይ የቆዳ በሽታ ታየ። 20ዐዛርያስና ሌሎቹም ካህናት በታላቅ ድንጋጤ የንጉሡን ግንባር ትኲር ብለው ተመለከቱ፤ ከቤተ መቅደስም እንዲወጣ አስገደዱት፤ ዖዝያም እግዚአብሔር እንደ ቀጣው ዐውቆ ለመውጣት ተጣደፈ።
21ንጉሥ ዖዝያ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የቆዳው በሽታ አለቀቀውም፤ ይህም በመሆኑ በተለየ ቤት ኖረ፤ ከእግዚአብሔርም ቤት እንዲገለል ተደረገ፤ ልጁ ኢዮአታም የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በመሆን የአገሪቱን ሕዝብ ያስተዳድር ነበር።
22ንጉሥ ዖዝያ በዘመነ መንግሥቱ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ መዝግቦት ይገኛል። 23ዖዝያ ሞተ፤ በነገሥታትም መካነ መቃብር አጠገብ ባለው ስፍራ ቀበሩት፤ በነገሥታት መካነ መቃብር ያልተቀበረው የቆዳ በሽታ ስለ ነበረበት ነው፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ። #ኢሳ. 6፥1።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997