የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26:14-21

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26:14-21 አማ54

ዖዝያንም ለጭፍራው ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቍርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው። በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚኖሩትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አደረገ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ። ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፤ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ። ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑአን የነበሩ ሰማኒያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ። ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ “ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብር አይሆንልህም” አሉት። ዖዝያንም ተቍጣ፤ የሚያጥንበትም ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቍጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ። ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፤ እነሆም፥ በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም አባርረሩት፤ እርሱም ደግሞ እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኮለ። ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤት ተቍርጦአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።