1 ወደ ጢሞቴዎስ 1:1-11

1 ወደ ጢሞቴዎስ 1:1-11 አማ05

በአዳኛችን በእግዚአብሔር፥ በተስፋችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ከጳውሎስ፦ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁንልህ። ወደ መቄዶንያ ስሄድ ሳለሁ ዐደራ እንዳልኩህ እዚያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ ታደርጋቸው ዘንድ በኤፌሶን ተቀመጥ። ወደ ተረትና መጨረሻ ወደሌለው ወደ ትውልዶች ቈጠራ እንዳይመለሱ እዘዛቸው፤ እነዚህ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉ እንጂ በእምነት ለሚደረገው ለእግዚአብሔር ሥራ አይጠቅሙም። የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብ፥ ከመልካም ኅሊና፥ ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው። አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ተለይተው ወደ ከንቱ ክርክር ተመልሰዋል። ይህንንም የሚያደርጉት የሕግ መምህራን ለመሆን ፈልገው ነው፤ ይሁን እንጂ የሚናገሩትን አያውቁም ወይም እርግጠኞች ነን የሚሉበትንም ነገር አያስተውሉም። ሰው በሚገባ ከሠራበት ሕግ መልካም መሆኑን እናውቃለን፤ እንዲሁም ሕግ የተሠራው ለደጋግ ሰዎች እንዳልሆነ እናውቃለን፤ ሕግ የተሠራው ለዐመፀኞችና ለወንጀለኞች፥ እግዚአብሔርን ለማያመልኩና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና መንፈሳዊ ነገርን ለሚንቁ፥ አባትንና እናትን ለሚገድሉና ለነፍሰ ገዳዮች፥ ለአመንዝሮችና ግብረ ሰዶምን ለሚያደርጉ፥ ሰውን አፍነው በመውሰድ ለሚሸጡ ነጋዴዎችና ለውሸታሞች፥ በሐሰት ለሚምሉና የእውነተኛ ትምህርት ተቃራኒ የሆነውን ነገር ሁሉ ለሚያደርጉ ነው፤ እውነተኛው ትምህርት ግን የሚገኘው ስለተመሰገነው እግዚአብሔር ከሚያበሥረው ክቡር ወንጌል ነው፤ ይህም ወንጌል ለእኔ በዐደራ የተሰጠኝ ነው።