1 ወደ ጢሞቴዎስ 1
1
1በአዳኛችን በእግዚአብሔር፥ በተስፋችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ከጳውሎስ፦
2በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፥
ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁንልህ። #ሐ.ሥ. 16፥1።
ከሐሰት ትምህርት ማስጠንቀቁ
3ወደ መቄዶንያ ስሄድ ሳለሁ ዐደራ እንዳልኩህ እዚያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ ታደርጋቸው ዘንድ በኤፌሶን ተቀመጥ። 4ወደ ተረትና መጨረሻ ወደሌለው ወደ ትውልዶች ቈጠራ እንዳይመለሱ እዘዛቸው፤ እነዚህ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉ እንጂ በእምነት ለሚደረገው ለእግዚአብሔር ሥራ አይጠቅሙም። 5የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብ፥ ከመልካም ኅሊና፥ ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው። 6አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ተለይተው ወደ ከንቱ ክርክር ተመልሰዋል። 7ይህንንም የሚያደርጉት የሕግ መምህራን ለመሆን ፈልገው ነው፤ ይሁን እንጂ የሚናገሩትን አያውቁም ወይም እርግጠኞች ነን የሚሉበትንም ነገር አያስተውሉም።
8ሰው በሚገባ ከሠራበት ሕግ መልካም መሆኑን እናውቃለን፤ 9እንዲሁም ሕግ የተሠራው ለደጋግ ሰዎች እንዳልሆነ እናውቃለን፤ ሕግ የተሠራው ለዐመፀኞችና ለወንጀለኞች፥ እግዚአብሔርን ለማያመልኩና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና መንፈሳዊ ነገርን ለሚንቁ፥ አባትንና እናትን ለሚገድሉና ለነፍሰ ገዳዮች፥ 10ለአመንዝሮችና ግብረ ሰዶምን ለሚያደርጉ፥ ሰውን አፍነው በመውሰድ ለሚሸጡ ነጋዴዎችና ለውሸታሞች፥ በሐሰት ለሚምሉና የእውነተኛ ትምህርት ተቃራኒ የሆነውን ነገር ሁሉ ለሚያደርጉ ነው፤ 11እውነተኛው ትምህርት ግን የሚገኘው ስለተመሰገነው እግዚአብሔር ከሚያበሥረው ክቡር ወንጌል ነው፤ ይህም ወንጌል ለእኔ በዐደራ የተሰጠኝ ነው።
ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት ያቀረበው ምስጋና
12እኔን ለአገልግሎት በመሾም ታማኝ አድርጎ የቈጠረኝንና የሰጠኝን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግናለሁ። 13ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን የሰደብኩና ያሳደድኩ፥ ያዋረድኩም ብሆን፤ እርሱ ምሕረት አደረገልኝ፤ እርሱም ይህን ምሕረት ያደረገልኝ እኔ ይህን ሁሉ ያደረግኹት ባለማወቅና ባለማመን ስለ ነበረ ነው። #ሐ.ሥ. 8፥3፤ 9፥4-5። 14የአምላካችን ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ የእኛ ከሆነው እምነትና ፍቅር ጋር ተትረፍርፎ ተሰጠኝ። 15“ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል እውነተኛና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ሁሉ የባስሁ ኃጢአተኛ እኔ ነኝ። 16ነገር ግን ምሕረት ተደረገልኝ፤ ምሕረት የተደረገልኝም ኢየሱስ ክርስቶስ ወሰን የሌለውን ትዕግሥቱን ከሁሉ የባስሁ ኀጢአተኛ በሆንኩት በእኔ ላይ በማሳየቱ በእርሱ ለሚያምኑና የዘለዓለም ሕይወት ለሚያገኙ ምሳሌ እንድሆን ነው። 17ስለዚህ ለዘለዓለማዊው ንጉሥ፥ ለማይሞተው፥ ለማይታየው፥ ለአንዱ አምላክ ክብርና ምስጋና ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን።
18ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! ከዚህ ቀደም ስለ አንተ በትንቢት በተነገረው መሠረት የሚከተለውን ትእዛዝ በዐደራ እሰጥሃለሁ፤ ትንቢቱን በመከተል መልካም ጦርነትን ተዋጋ፤ 19እምነትና መልካም ኅሊና ይኑርህ። አንዳንድ ሰዎች ኅሊናቸውን በመጣላቸው መርከብ በማዕበል እንደሚጠፋ እምነታቸውን አጥፍተዋል። 20ከእነርሱ መካከል ሄሜኔዎስና እስክንድር ይገኛሉ፤ እነርሱ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ከመናገር መቈጠብን እንዲማሩ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁ።
Currently Selected:
1 ወደ ጢሞቴዎስ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997