1 ተሰሎንቄ ሰዎች 2:13-20

1 ተሰሎንቄ ሰዎች 2:13-20 አማ05

ደግሞም ስለ እናንተ ሳናቋርጥ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ምክንያት አለን፤ ይኸውም ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ በእናንተ በአማኞች የሚሠራውን ይህንን ቃል የተቀበላችሁት እንደ ሰው ቃል ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጋችሁ ነው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል ነው። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተም በይሁዳ ምድር የሚገኙትን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያን የሆኑትን አርአያ ተከትላችኋል፤ እነርሱ በአይሁድ መከራ እንደ ደረሰባቸው ሁሉ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራ ደርሶባችኋል። አይሁድ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን የገደሉ እኛንም አሳደው ከአገር ያስወጡ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑና ሰዎችን ሁሉ የሚጠሉ ናቸው፤ አሕዛብ የሚድኑበትን ቃል እንዳንናገር እንኳ ይከለክሉናል፤ በዚህ ዐይነት ኃጢአትን በኃጢአት ላይ እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ስለዚህ በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቊጣ መጥቶባቸዋል። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ በመለየታችን ስለ እናንተ ያለን ናፍቆት ብዙ ስለ ሆነ በዐይነ ሥጋ ልናያችሁ ብዙ ጥረት አደረግን። ወደ እናንተ መምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ወደ እናንተ ለመምጣት ደጋግሜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን ከለከለን። ታዲያ፥ ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የምንመካበት የድል አክሊላችን እናንተ አይደላችሁምን? በእርግጥ ክብራችንና ደስታችን እናንተ ናችሁ።