1 ተሰሎንቄ 2:13-20

1 ተሰሎንቄ 2:13-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። እናንተ ወንድሞች ሆይ! በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና። እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ፤ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፤ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፤ ሁልጊዜ ኀጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል። እኛ ግን ወንድሞች ሆይ! በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፤ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን። ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።

1 ተሰሎንቄ 2:13-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ሳይሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ስለ ተቀበላችሁ፣ ደግሞም እውነት ነው፤ እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ እናመሰግናለን፤ ይኸውም ቃል በእናንተ ዘንድ የሚሠራ ነው። ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን በይሁዳ የሚገኙትን የእግዚአብሔርን አብያተ ክርስቲያናት መስላችኋል፤ እነዚያ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፣ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራን ተቀብላችኋል። እነርሱ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም አሳደዱን፤ እግዚአብሔርንም ደስ አላሠኙትም፤ የሰውም ሁሉ ፀር ሆኑ፤ ይኸውም ይድኑ ዘንድ ለአሕዛብ እንዳንናገር ለመከልከል ነው፤ በዚህ ሁኔታ ኀጢአታቸውን ሁልጊዜ በራሳቸው ላይ እስከ መጨረሻው እያከማቹ ይሄዳሉ። ቍጣውም በእነርሱ ላይ ያለ ልክ መጥቷል። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ እኛ በልባችን ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ብንለይም፣ ለእናንተ ካለን ታላቅ ናፍቆት የተነሣ ፊታችሁን ለማየት ብርቱ ጥረት አደረግን። ወደ እናንተ ለመምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን አዘገየን። ጌታችን ኢየሱስ ሲመጣ በርሱ ፊት ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም አክሊላችን ማን ነው? እናንተ አይደላችሁምን? በርግጥ እናንተ ክብራችንም ደስታችንም ናችሁ።

1 ተሰሎንቄ 2:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና። እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥ ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል። እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን። ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።

1 ተሰሎንቄ 2:13-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደግሞም ስለ እናንተ ሳናቋርጥ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ምክንያት አለን፤ ይኸውም ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ በእናንተ በአማኞች የሚሠራውን ይህንን ቃል የተቀበላችሁት እንደ ሰው ቃል ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጋችሁ ነው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል ነው። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተም በይሁዳ ምድር የሚገኙትን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያን የሆኑትን አርአያ ተከትላችኋል፤ እነርሱ በአይሁድ መከራ እንደ ደረሰባቸው ሁሉ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራ ደርሶባችኋል። አይሁድ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን የገደሉ እኛንም አሳደው ከአገር ያስወጡ ናቸው፤ እነርሱ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑና ሰዎችን ሁሉ የሚጠሉ ናቸው፤ አሕዛብ የሚድኑበትን ቃል እንዳንናገር እንኳ ይከለክሉናል፤ በዚህ ዐይነት ኃጢአትን በኃጢአት ላይ እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ስለዚህ በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቊጣ መጥቶባቸዋል። ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! በመንፈስ ሳይሆን በሥጋ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ በመለየታችን ስለ እናንተ ያለን ናፍቆት ብዙ ስለ ሆነ በዐይነ ሥጋ ልናያችሁ ብዙ ጥረት አደረግን። ወደ እናንተ መምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ወደ እናንተ ለመምጣት ደጋግሜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን ከለከለን። ታዲያ፥ ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የምንመካበት የድል አክሊላችን እናንተ አይደላችሁምን? በእርግጥ ክብራችንና ደስታችን እናንተ ናችሁ።

1 ተሰሎንቄ 2:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህም የመልእክትን ቃል፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በአማኞች ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። እናንተ ወንድሞች ሆይ! በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከወገኖቻችሁ ተቀብላችኋልና። እነዚያም ጌታን ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም ደግሞ አሳደዱ፤ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፤ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፤ ለአሕዛብ እንዳንናገር በመከልከል እነርሱ እንዳይድኑ ያደርጋሉ፤ በዚህም ያለማቋረጥ የኃጢአታቸውን መስፈርያ ይሞላሉ፤ ነገር ግን በመጨረሻ የእግዚአብሔር ቁጣው ይመጣባቸዋል። እኛ ግን ወንድሞች ሆይ! በልብ ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ብናጣችሁም፥ በብዙ ናፍቆት ግን ፊታችሁን ለማየት እጅግ ጓጓን፤ ወደ እናንተ ልንመጣ ፈልገን ነበርና፤ በእርግጥም እኔ ጳውሎስ አንድና ሁለት ጊዜ ሞክሬ ነበር፥ ሰይጣን ግን መሰናክል ሆነብን። ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በፊቱ የተስፋችን ወይም የደስታችን ወይም የመመክያችን አክሊል ምንድነው? እናንተ አይደላችሁምን? እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።