የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8:7-22

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8:7-22 አማ05

እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ የሚሉህን ነገር ሁሉ ተቀበል፤ እነርሱ የናቁት አንተን አይደለም፤ በእነርሱ ላይ ነግሼ እንዳልኖር፥ እነርሱ የናቁት እኔን ነው። እኔ እነርሱን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ፊታቸውን መልሰው ከእኔ በመራቅ ባዕዳን አማልክትን ሲያመልኩ ኖረዋል፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ሁሉ እነሆ በአንተም ላይ መፈጸም ጀምረዋል፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ የሚሉህን ተቀበል፤ ነገር ግን ንጉሦቻቸው ወደ ፊት በእነርሱ ላይ የሚፈጽሙባቸውን ነገር ሁሉ በመግለጥ በብርቱ አስጠንቅቃቸው።” ሳሙኤልም ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ እግዚአብሔር የነገረውን ሁሉ አስረዳቸው፤ እንዲህም ሲል ገለጠላቸው፤ “ንጉሣችሁ የሚያደርግባችሁ ነገር ይህ ነው፦ ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ አንዳንዶቹም በሠረገሎቹም ፊት የሚሮጡ ያደርጋቸዋል፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹን የሺህ አለቆችና የኀምሳ አለቆች አድርጎ ይሾማል፤ ወንዶቹ ልጆቻችሁ የንጉሡ ሁዳድ አራሾችና መከር ሰብሳቢዎች ይሆናሉ፤ ሌሎችም የጦር መሣሪያና የሠረገላ ዕቃ ሠራተኞች ይሆናሉ። ሴቶች ልጆቻችሁም ለእርሱ ሽቶ አዘጋጀች፥ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ይሆናሉ። ምርጥ የሆነውን የእርሻ መሬታችሁን፥ የወይን ተክል ቦታችሁንና የወይራ ተክላችሁን ሁሉ ወስዶ ለባለሟሎቹ ይሰጥባችኋል። ከእህላችሁና ከወይናችሁም ከዐሥር አንዱን እጅ ወስዶ ለቤተ መንግሥቱ ባለሟሎችና አጃቢዎች ይሰጥባችኋል። የወንድና የሴት አገልጋዮቻችሁን፥ ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ወስዶ ለራሱ መጠቀሚያ ያደርጋቸዋል። ከበግና ከፍየል መንጋዎቻችሁ ከዐሥር አንዱን ይወስዳል፤ እናንተም የእርሱ ባሪያዎች ትሆናላችሁ፤ ያ ዘመን በደረሰ ጊዜ የመረጣችሁት ንጉሥ ስለሚፈጽምባችሁ በደል በመረረ ሁኔታ ማጒረምረም ትጀምራላችሁ፤ እግዚአብሔር ግን አቤቱታችሁን አያዳምጥም።” ይሁን እንጂ ሕዝቡ ሳሙኤል ለነገራቸው ቃል ሁሉ ዋጋ አልሰጡትም፤ ይልቁንም “እንደዚህ አይደለም! እኛ ንጉሥ እንዲኖረን እንፈልጋለን፤ በዚህም ዐይነት ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት እኛን የሚያስተዳድርና ከጠላቶቻችንም ጋር በምንዋጋበት ጊዜ ወደ ጦር ሜዳ የሚመራን ንጉሥ ይኖረናል።” ሳሙኤልም እነርሱ ያሉትን ሁሉ አዳመጠ፤ ከዚያም ሄዶ ለእግዚአብሔር ነገረ፤ እግዚአብሔርም “እነርሱ በጠየቁህ መሠረት፥ ንጉሥ አንግሥላቸው” አለው፤ ከዚያም በኋላ ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ሳሙኤል ሕዝቡን አሰናበተ።