እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ ስማ። ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ዕለት አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን በማምለክ ያደረጉትን ሁሉ በአንተም ላይ እያደረጉ ነው። አሁን የሚሉህን ስማቸው፤ በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንደሚፈጽምባቸውም አሳውቃቸው፤ በሚገባም አስጠንቅቃቸው።” ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ፣ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ ተናገረ። እንዲህም አለ፤ “በላያችሁ የሚነግሠው ንጉሥ የሚያደርግባችሁ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሠረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ። አንዳንዶቹን ሻለቆችና ዐምሳ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ ሌሎቹን መሬቱን እንዲያርሱና እህሉን እንዲያጭዱ፣ የቀሩትን ደግሞ የጦር መሣሪያና ለሠረገላ የሚሆኑትን ዕቃዎች እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቱ ቀማሚ፣ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል። ከዕርሻችሁ፣ ከወይንና ከወይራ ተክል ቦታዎቻችሁ ምርጥ ምርጡን ወስዶ ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ከእህላችሁና ከወይናችሁ ከዐሥር አንዱን ወስዶ ለሹማምቱና ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ወንድና ሴት አሽከሮቻችሁን እንዲሁም ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ለራሱ ያደርጋቸዋል። ከበግና ከፍየል መንጎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ለራሱ ይወስዳል፤ እናንተ ራሳችሁም ባሪያዎቹ ትሆናላችሁ። ያም ቀን በደረሰ ጊዜ፣ ወዳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ ነገር ግን በዚያ ቀን እግዚአብሔር አይመልስላችሁም።” ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን መስማት እንቢ በማለት፤ እንዲህ አሉ፤ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን፤ እኛም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች የሚመራንና ከፊታችን የሚሄድ፣ ጦርነታችንንም የሚዋጋልን ንጉሥ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን።” ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሰማ፤ ያንኑ በእግዚአብሔር ፊት ተናገረው። እግዚአብሔርም፣ “የሚሉህን ስማቸው፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው። ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፣ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።
1 ሳሙኤል 8 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 8:7-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos