የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18:1-16

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18:1-16 አማ05

ሳኦልና ዳዊት ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ የሳኦል ልጅ ዮናታን ከዳዊት ጋር እጅግ የተቀራረበ አንድነት መሠረተ፤ እንደ ራሱም አድርጎ ወደደው፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ከእርሱ ጋር እንዲኖር አደረገ፤ ወደ ቤቱም እንዲሄድ አላሰናበተውም፤ ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ ስለ ወደደው ከእርሱ ጋር የወዳጅነት ቃል ኪዳን ገባ፤ የለበሰውንም ካባ አውልቆ ለዳዊት ሰጠው፤ እንዲሁም የጦር ልብሱን፥ ሰይፉን፥ ቀስቱንና መታጠቂያውን ጭምር ሰጠው። ሳኦል በትእዛዝ በሚያዘምትበት ቦታ ሁሉ የዳዊት ተልእኮ የተሳካ ሆነ፤ ስለዚህም ሳኦል በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የመኰንንነት ማዕርግ እንዲኖረው አደረገ፤ ይህም የሳኦልን የጦር መኰንኖችና ወታደሮችን ሁሉ አስደሰተ። ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ሲመለስና ወታደሮችም ወደየቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ፥ በእስራኤል በሚገኙት ከተሞች ሁሉ የሚኖሩ ሴቶች ሳኦልን ለመቀበል ወጡ፤ እነርሱም በእልልታ እየዘፈኑና እየጨፈሩ፥ የመስንቆ ድምፅ እያሰሙ አታሞ ይመቱ ነበር። ሴቶቹም ባደረጉት የአቀባበል ሥርዓት ላይ “ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገዳይ!” እያሉ ዘፈኑ። ሳኦል ይህ አባባል ደስ ስላላሰኘው በጣም ተቈጥቶ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ፥ ለእኔ ግን አንድ ሺህ ብቻ ሰጡ፤ እንግዲህ ከመንገሥ በቀር ምን ቀረው!” አለ። ከዚህም የተነሣ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ ቅናትና ጥርጣሬ አደረበት። በማግስቱም በድንገት ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ በቤቱም ውስጥ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ በነበረው ዐይነት ለሳኦል በገና ይደረድርለት ነበር፤ ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። “መትቼ ከግድግዳ ጋር አጣብቀዋለሁ!” ብሎ በልቡ አሰበ፤ ከዚህም በኋላ ጦሩን በዳዊት ላይ ሁለት ጊዜ ወረወረ፤ ዳዊት ግን ሁለቴም ዞር እያለ አመለጠ። እግዚአብሔር እርሱን ትቶ ከዳዊት ጋር ስለ ነበረ ሳኦል ዳዊትን ፈራው፤ ከዚህም የተነሣ ሳኦል ዳዊትን ከፊቱ ለማራቅ የሺህ ወታደሮች አዛዥ አድርጎ ላከው፤ ዳዊትም ወታደሮቹን ወደ ጦርነት መራ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። ሳኦልም የዳዊትን ተልእኮ መሳካት እየተመለከተ በይበልጥ ይፈራው ጀመር፤ ነገር ግን ተልእኮው የሚሳካለት መሪ በመሆኑ በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ የሚገኝ ሕዝብ ሁሉ ዳዊትን ይወድ ነበር፤