አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 6
6
የሰሎሞን ቤተ መቅደሱን መሥራት መጀመር
1የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጡ ከአራት መቶ ሰማኒያ ዓመት በኋላ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ፤ 2ቤተ መቅደሱ በውስጥ በኩል ርዝመቱ ኻያ ሰባት ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ 3በመግቢያው በር የሚገኘው በረንዳ ቁመቱ አራት ሜትር ተኩል፥ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ዘጠኝ ሜትር ነበር። 4ለቤተ መቅደሱም ሕንጻ ከውስጥ ሰፋ፥ ከውጪ ጠበብ ያሉ መስኮቶች ነበሩት፤ 5የቤተ መቅደሱን ሕንጻ አስጠግቶ በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ክፍሎችን አደረገ። 6የታችኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር፥ የሁለተኛው ፎቅ ክፍል ወርድ ሁለት ሜትር ከሰባ ሳንቲ ሜትር፥ የመጨረሻው ፎቅ ክፍል ወርድ ሦስት ሜትር ከዐሥር ሳንቲ ሜትር ነበር፤ የእያንዳንዱ ወለል ግንብ ከታች በኩል ካለው የወለል ግንብ የሳሳ ነበር፤ ሠረገሎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ግድግዳ እንዳይገቡ ለማድረግ ከቤተ መቅደሱ ግድግዳ ውጪ ዐረፍቶችን አደረገ።
7ቤተ መቅደሱ የታነጸባቸው ድንጋዮች ተጠርበው የተዘጋጁት፤ በዚያው በተፈለጡበት ቦታ ነበር፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሚሠራበት ጊዜ የመዶሻ፥ የመጥረቢያ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ አይሰማም ነበር።
8ተጨማሪ ሆኖ የተሠራው ሕንጻ የታችኛው ፎቅ መግቢያ በር የሚገኘው ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ በኩል ነበር፤ እርሱም ከሁለተኛውና ከሦስተኛው ፎቅ ጋር የሚያገናኙት ደረጃዎች ነበሩት። 9በዚህ አኳኋን ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሥራ ፈጸመ፤ ጣራውንም ከውስጥ በኩል ከሊባኖሱ ዛፍ እንጨት በተሠራ አግዳሚ ሠረገላና ጠርብ ለበደው። 10የእያንዳንዱ ፎቅ ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ሆኖ ከውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ተጠግቶ የተሠራው ባለ ሦስት ፎቅ ተጨማሪ ሕንጻ ከዋናው ሕንጻዎች ከሊባኖስ ዛፍ በተሠሩት አግዳሚ ሠረገሎች የተያያዘ ነበር።
11እግዚአብሔር ሰሎሞንን እንዲህ አለው፦ 12-13“ሕጎቼን፥ ትእዛዞቼንና ሥርዓቴን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል ለአንተ አጸናለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ሆኜ አንተ በምትሠራው በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ እኖራለሁ። ከቶም አልለያቸውም።”
14በዚህ ዐይነት ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ።
የቤተ መቅደሱ የውስጥ አሠራር
(2ዜ.መ. 3፥8-14)
15የቤተ መቅደሱ ግንብ ከውስጥ በኩል ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርበው በተሠሩ ሳንቃዎች ተለበደ፤ የወለሉም ጣውላ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር። 16ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራ አንድ ውስጣዊ ክፍል ከቤተ መቅደሱ በስተ ኋላ ገባ ብሎ ተሠራ፤ የእርሱም ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተከፈለ ነበር፤ #ዘፀ. 26፥33-34። 17ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የሚገኘውም የተቀደሰ ክፍል ርዝመት ዐሥራ ስምንት ሜትር ነበር፤ 18የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሳንቃዎች በአበባ እንቡጦችና በፈኩ አበባዎች ቅርጽ አጊጠው ነበር፤ ውስጡም ሁሉ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ ስለ ተለበደ የግንቡ ድንጋዮች አይታዩም ነበር።
19ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በስተ ኋላ በኩል የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት የሚቀመጥበት ውስጣዊ ክፍል ተሠራ። 20ይህም ውስጣዊ ክፍል ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ሲሆን በሙሉ በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ነበር፤ መሠዊያውም ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። 21ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ እርሱም በወርቅ በተለበጠው ውስጠኛ ክፍል መግቢያ በር ክፈፉንም በተሸጋገሩ የወርቅ ሰንሰለቶች አስጌጠው። 22በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የሚገኘውን መሠዊያ ጭምር መላውን ቤተ መቅደስ ከውስጥ በኩል በወርቅ ለበጠው። #ዘፀ. 30፥1-3።
23የእያንዳንዳቸው ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የሆነ፥ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ሥዕሎች በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ሠራ። 24-25የሁለቱም ኪሩቤል ቅርጽና መጠን ተመሳሳይ ነበር፤ እያንዳንዱም ኪሩቤል ሁለት ክንፎች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ክንፍ ርዝመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን፥ ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ድረስ ያለው ርዝመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ 26የየአንዳንዱ ኪሩብ ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር ነበር። 27ኪሩቤልንም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲቆሙ አደረገ፤ ስለዚህም የተዘረጉ ሁለቱ ክንፎቻቸው በክፍሉ መካከለኛ ቦታ ላይ ተገናኝተው ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ በተዘረጉበት አቅጣጫ ግንቦቹን ይነኩ ነበር። 28ሁለቱንም ኪሩቤል በወርቅ ለበጣቸው። #ዘፀ. 25፥18-20።
29የዋናውን ክፍልና የውስጠኛውን ክፍል ግንቦች በሙሉ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ 30እርሱም ከውስጥና ከውጪ በኩል ያሉትን ክፍሎች ወለል እንኳ በወርቅ ለበጣቸው።
31ከወይራ እንጨት የተሠራ ሁለት ተከፋች በር በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ እንዲቆም አደረገ፤ በሩም አምስት ማእዘን ያለው ሆኖ አናቱ ላይ ቀጥ ብሎ የተሠራ ቅስት ነበር። 32ሁለቱን በሮች በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ እርሱም በሮቹን፥ ኪሩቤልን፥ የዘንባባ ዛፎቹን፥ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው። 33እንዲሁም ወደ ዋናው ክፍል ለሚያደርሰው መግቢያ በር ከወይራ እንጨት የተሠራ ባለ አራት ማእዘን ክፈፍ አበጀለት። 34ሁለቱንም በሮች ከዝግባ እንጨት ሠራ፤ አንዱ በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፤ ሁለተኛውም በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። 35እነርሱንም ሙሉ በሙሉ በወርቅ በተለበጡ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው።
36በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አንድ የውስጥ አደባባይ ሠራ፤ በዚህም አደባባይ ዙሪያ በየሦስቱ ዙር የድንጋይ ረድፍ አንድ የሊባኖስ ዛፍ ሠረገላ ሳንቃ የተጋደመበት ግንብ አደረገ።
37ይህም ቤተ መቅደስ መሠረቱ የተጣለው ሰሎሞን በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር ነበር። 38ሰሎሞን በነገሠ በዐሥራ አንደኛ ዓመቱ፥ ቡል ተብሎ በሚጠራው በስምንተኛው ወር ላይ የቤተ መቅደሱ ሥራ ልክ በታቀደው መሠረት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ሰባት ዓመት ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997