አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 5
5
የሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት መዘጋጀት
(2ዜ.መ. 2፥1-18)
1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ከዳዊት ጋር ወዳጅነቱን አጽንቶ ቈይቶ ነበር፤ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት እግር መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ መልእክተኞቹን ላከ፤ 2ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፤ 3“አባቴ ዳዊት በዙሪያው ከነበሩት የጠላት አገሮች ሠራዊት ጋር ሲዋጋ መኖሩን አንተ ራስህ ታውቀዋለህ፤ በጠላቶቹ ላይ ድልን እስኪያጐናጽፈው ድረስ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት አለመቻሉንም ታስታውሳለህ፤ 4አሁን ግን አምላኬ እግዚአብሔር በሀገሬ ድንበር ዙሪያ ሁሉ ሰላም ሰጥቶኛል፤ ምንም ዐይነት አደጋ የሚጥል ጠላት የለብኝም፤ 5እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት ‘ከአንተ በኋላ የማነግሠው ልጅህ ለእኔ ቤተ መቅደስ ይሠራልኛል’ ሲል ተስፋ ሰጥቶት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት እነሆ፥ አሁን ወስኛለሁ፤ #2ሳሙ. 7፥12-13፤ 1ዜ.መ. 17፥11-12። 6ስለዚህ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት የሚቈርጡ ሰዎችን ወደ ሊባኖስ ላክልኝ፤ የእኔም ሰዎች ከእነርሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ አደርጋለሁ፤ ለሰዎችህም አንተ የምትወስነውን ደመወዝ እከፍላለሁ፤ አንተ እንደምታውቀው የእኔ ሰዎች ስለ ዛፍ አቈራረጥ የአንተን ሰዎች ያኽል ዕውቀት የላቸውም።”
7ኪራም የሰሎሞን መልእክት ሲደርሰው እጅግ ስለ ተደሰተ፥ “በእርሱ እግር ተተክቶ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ እንዲነግሥ ይህን የመሰለ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን!” አለ፤ 8ከዚህ በኋላ ኪራም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለሰሎሞን ላከ “ያስተላለፍከው መልእክት ደርሶኛል፤ አንተ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፤ የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባውን ግንድ አዘጋጅቼ አቀርብልሃለሁ፤ 9የእኔ ሰዎችም ግንዶቹን ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዳሉ፤ አንድነት ጠፍረው አስረውም አንተ ወደምትመርጠው ጠረፍ ተንሳፍፈው እንዲደርሱ ያደርጋሉ፤ በዚያም የእኔ ሰዎች ማሰሪያውን ፈተው ለአንተ ሰዎች ያስረክቡአቸዋል፤ አንተም በበኩልህ በቤተ መንግሥቴ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምግብ በመላክ ፍላጎቴን ታረካለህ።”
10በዚህ ዐይነት ኪራም ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖሱን ዛፍና የዝግባ ግንድ ሁሉ አቀረበለት፤ 11ሰሎሞንም በበኩሉ በኪራም ቤተ መንግሥት ውስጥ ላሉት ሰዎች ቀለብ የሚሆን ሁለት ሺህ ቶን ስንዴና አራት መቶ ሺህ ሊትር ንጹሕ የወይራ ዘይት በየዓመቱ ይሰጥ ነበር።
12እግዚአብሔር አስቀድሞ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞን መካከል ሰላም ስለ ነበረ ሁለቱም የጋራ ስምምነት ውል አደረጉ።
13ንጉሥ ሰሎሞን ከመላው እስራኤል ሠላሳ ሺህ የግዳጅ ሠራተኞችን መለመለ፤ 14በእነርሱ ላይ አዶኒራም የተባለውን ሰው ኀላፊ አድርጎ ሾመ፤ ሠራተኞቹንም ዐሥር ዐሥር ሺህ አድርጎ በሦስት ቡድን በመክፈል እያንዳንዱ ቡድን ተራ ገብቶ አንድ ወር በሊባኖስ እንዲሠራ፥ ሁለት ወር ደግሞ በቤቱ እንዲያርፍ ወሰነ። #1ነገ. 12፥18። 15ንጉሥ ሰሎሞን በኮረብታማው አገር ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማኒያ ሺህ፥ የተፈለጠውን ድንጋይ ተሸክመው የሚያመጡ ሰባ ሺህ ሰዎችን መደበ፤ 16የእነዚህ ሠራተኞች የበላይ ሆነው ሥራውን የሚቈጣጠሩ ሦስት ሺህ ሦስት መቶ ሰዎችን አዘጋጀ፤ 17በዚህ ዐይነት ሠራተኞቹ በንጉሥ ሰሎሞን ትእዛዝ ለቤተ መቅደሱ መሠረት የሚሆን ታላላቅ ድንጋዮችን ፈለጡ። 18የሰሎሞንና የኪራም ጥበበኞች ሠራተኞችና እንዲሁም የቢብሎስ ሰዎች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የሚያስችላቸውን ድንጋይና እንጨት ሁሉ አዘጋጁ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997