አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 4
4
ሰሎሞን የሾማቸው ባለሥልጣኖች
1ንጉሡ ሰሎሞን በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ 2የሾማቸው ባለሥልጣኖች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፥ እነርሱም፦
ዓዛርያስ የተባለው የሳዶቅ ልጅ፦ ካህን፤
3ኤሊሖሬፍና አኪያ የተባሉት የሺሻ ልጆች፥ የቤተ መንግሥት ጸሐፊዎች፤
ኢዮሣፍጥ የተባለው የአሒሉድ ልጅ፥ ታሪክ ጸሐፊና የመዛግብት ኀላፊ፤
4በናያ የተባለው የዮዳሄ ልጅ፦ የጦር ሠራዊት አዛዥ፤
ሳዶቅና አብያታር፦ ካህናት፤
5ዓዛርያስ የተባለው የናታን ልጅ፦
የክፍላተ ሀገር ገዢዎች የበላይ ኀላፊ፤
የናታን ልጅ ካህኑ ዛቡድ፦ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ፤
6አሒሻር የተባለው፦ የቤተ መንግሥት አገልጋዮች ኀላፊ፤
አዶኒራም የተባለው የዓብዳ ልጅ፦ የግዳጅ ሥራ ተቈጣጣሪ ነበሩ።
7ሰሎሞን በመላው እስራኤል ዐሥራ ሁለት የክፍላተ ሀገር ገዢዎችን ሾመ፤ የእነርሱም ተግባር ከየግዛታቸው ለንጉሡና ለንጉሡ ቤተሰብ ቀለብ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ማቅረብ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም በዓመት ውስጥ ለአንድ ወር ቀለብ የማቅረብ ግዴታ ነበረባቸው። 8የእነዚህም ዐሥራ ሁለት የክፍላተ ሀገር ገዢዎችና የሚያስተዳድሩአቸውም ግዛቶች ስም ዝርዝር ከዚህ የሚከተለው ነው፥
ቤንሑር፦ ኰረብታማ የሆነችው የኤፍሬም አገር ገዢ፤
9ቤንዴቀር፦ የማቃጽ፥ የሻዓልቢም፥ የቤትሼሜሽ፥ የኤሎንና የቤት ሐናን ከተሞች ገዥ፤
10ቤንሔሴድ፦ የአሩቦትና የሶኮ ከተሞች፥ እንዲሁም የመላው የሔፌር ግዛት አስተዳዳሪ፤
11ጣፋት የተባለችውን የሰሎሞንን ሴት ልጅ አግብቶ የነበረው ቤን አሚናዳብ የመላው የዶር ግዛት አስተዳዳሪ፤
12በዓና የተባለው የአሒሉድ ልጅ፦ የታዕናክና የመጊዶ ከተሞች፥ እንዲሁም በቤትሻን አጠገብ ያለው ግዛት በሙሉ፥ በጻርታን ከተማ አጠገብ ያለው ግዛትና በኢይዝራኤል ከተማ በስተደቡብ ያለው ግዛት፥ እንዲሁም አቤልመሖላና ዮቅመዓም ተብለው እስከሚጠሩት ከተሞች ድረስ ያለው ግዛት ሁሉ አስተዳዳሪ፤
13በገለዓድ ራሞት ቤን ጌቤር ተብላ የምትጠራው ከተማ፥ በገለዓድ የምናሴ ዘር የሆነው የያኢር ጐሣ ይዞታዎች የሆኑት መንደሮች፥ በባሳን አርጎብ ተብላ የምትጠራው ግዛት፥ እንዲሁም በሮቻቸው የነሐስ መወርወሪያ ባሉአቸው የቅጽር ግንቦች የተመሸጉ በድምሩ የስድሳ ታላላቅ መንደሮች አስተዳዳሪ፤
14አሒናዳብ የተባለው የዒዶ ልጅ፦ የማሕናይም ክፍለ ሀገር ገዢ፤
15ከሰሎሞን ሴቶች ልጆች መካከል ባስማት ተብላ የምትጠራውን አግብቶ የነበረ አሒመዓጽ፦ የንፍታሌም ግዛት አስተዳዳሪ፤
16በዓና የተባለው የሑሻይ ልጅ፦ የአሴር ግዛትና የበዓሎት ከተማ ገዢ፤
17ኢዮሣፍጥ የተባለው የፋሩሕ ልጅ፦ የይሳኮር ግዛት አስተዳዳሪ፤
18ሳሚ የተባለው የኤላ ልጅ፦ የብንያም ግዛት አስተዳዳሪ፤
19ጌቤር የተባለው የኡሪ ልጅ፦ በአሞራውያን ንጉሥ ሲሖንና በባሳን ንጉሥ ዖግ ትገዛ የነበረችው የገለዓድ ግዛት አስተዳዳሪ።
እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን አስተዳዳሪዎች የሚቈጣጠር በመላ አገሪቱ ሌላ አንድ የበላይ ኀላፊ ነበር።
ብልጽግና የሞላበት የሰሎሞን መንግሥት
20የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ብዛት እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ነበር፤ እነዚህ ሁሉ እየበሉና እየጠጡ ዘወትር ደስ ይሰኙ ነበር፤ #ዘፍ. 15፥8፤ 2ዜ.መ. 9፥26። 21የሰሎሞንም ግዛት ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ግዛት፥ ከዚያም አልፎ እስከ ግብጽ ወሰን ያለውን አገር ሁሉ ያጠቃልል ነበር፤ የእነዚህም አገሮች ሕዝቦች በጠቅላላ ሰሎሞን በነበረበት ዘመን ሁሉ ለእርሱ ተገዢዎች ሆነው ይገብሩለት ነበር።
22ሰሎሞንም በየቀኑ ለቀለብ የሚሆን አምስት ሺህ ኪሎ ያኽል ምርጥ ዱቄት፥ ዐሥር ሺህ ኪሎ ያኽል መናኛ ዱቄት፥ 23በበረት ውስጥ እየተመገቡ የደለቡ ዐሥር ሰንጋዎችና በግጦሽ መስክ ተሰማርተው የተመገቡ ኻያ ፍሪዳዎችና አንድ መቶ በጎች፥ ከዚህም ሌላ አጋዘኖች፥ የሜዳ ፍየሎች፥ ሚዳቋዎችና ምርጥ ወፎች ያስፈልጉት ነበር።
24ሰሎሞን ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ ያለውን ምድር ሁሉ ከቲፍሳሕ ከተማ ጀምሮ እስከ ጋዛ ከተማ ድረስ ይገዛ ነበር፤ ይህም ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚገኙትን ነገሥታት ሁሉ ያጠቃልላል፤ ጐረቤቱ ከሆኑት አገሮችም ሁሉ ጋር በሰላም ይኖር ነበር። 25በኖረበትም ዘመን ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ መላው የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ያለስጋት በሰላም ይኖር ነበር፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ የራሱ የሆነ የወይን ተክልና የበለስ ዛፍ ስለ ነበረው በእነዚህ ተክሎች ጥላ ሥር ያርፍ ነበር።
26ሰሎሞን ሠረገላ የሚስቡ አርባ ሺህ ቅልብ ፈረሶችና ለጦርነት የሚያገለግሉ ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት፤ #1ነገ. 10፥26፤ 2ዜ.መ. 1፥14፤ 9፥25። 27ለሰሎሞንና በቤተ መንግሥቱ ለሚቀለቡት ሁሉ የሚያስፈልገውን ምግብ የሚያቀርቡት ዐሥራ ሁለቱ የክፍላተ ሀገር ገዢዎች እያንዳንዳቸው በተመደበላቸው ወር ምንም ነገር ሳያጓድሉ በወቅቱ ያመጡ ነበር። 28ከዚህም በቀር እያንዳንዱ ገዢ እንደአስፈላጊነቱ የሚደርስበትን ሠረገላ ለሚስቡ ፈረሶችና ሌላም አገልግሎት ለሚያበረክቱ የጋማ ከብቶች ገብስና ገፈራ ያቀርብ ነበር።
ለሰሎሞን የተሰጠ ጥበብ
29እግዚአብሔር ለሰሎሞን እጅግ አስደናቂ የሆነ ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሁም ወሰን የማይገኝለትን ዕውቀት ሰጠው፤ 30ሰሎሞን ከምሥራቅ አገርና ከግብጽም ጥበበኞች እጅግ የላቀ ጥበብ ነበረው፤ 31እርሱ ከሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ጥበበኛ ነበረ፤ ከኤዝራሐዊው ኤታን፥ የማሖል ልጆች ከሆኑት ከሄማን፥ ከካልኮልና ከዳርዓዕ የሚበልጥ ጥበበኛ ነበረ፤ ዝናውም ከፍ ብሎ በጐረቤት ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ አስተጋባ፤ #መዝ. 89። 32ሦስት ሺህ ምሳሌዎችንና አንድ ሺህ አምስት የመዝሙር ድርሰቶችን ደረሰ፤ #ምሳ. 1፥1፤ 10፥1፤ 25፥1። 33ሰሎሞን ሊባኖስ ዛፍ ጀምሮ በቤት ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ድረስ ስለ ዛፎችና ስለ ተክሎች እየመሰለ ተናግሮአል፤ እንዲሁም ስለ ልዩ ልዩ እንስሶች፥ ስለ ወፎች በሆዳቸው እየተሳቡ ስለሚሄዱ ፍጥረቶችና ስለ ዓሣዎችም አስተምሮአል። 34በመላው ዓለም የሚገኙ ነገሥታት ስለ ሰሎሞን ጥበብ ሰምተው የእርሱን ጥበብ ያዳምጡ ዘንድ መልእክተኞቻቸውን ይልኩ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997