የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 18:18-40

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 18:18-40 አማ05

ኤልያስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእግዚአብሔርን ትእዛዞች በመጣስ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው የባዕድ አምላክ ምስሎች በመስገድ ችግር የምታመጡ አንተና የአባትህ ቤተሰብ ናችሁ እንጂ እኔ በእስራኤል ላይ ችግር የማመጣ አይደለሁም! ይልቅስ አሁን እስራኤላውያንን ሁሉ እንዳገኛቸው በቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብልኝ፤ በንግሥት ኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ ኀምሳ የባዓል ነቢያትንና አራት መቶ የአሼራ ነቢያትን ጭምር ይዘህ ና።” ስለዚህም አክዓብ ለእስራኤላውያን ሁሉና ለነቢያት በሙሉ ጥሪ አድርጎ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበሰቡ አስደረገ። ኤልያስም ወጥቶ ለሰዎቹ፦ “እስከ መቼ ድረስ በሁለት ልብ ስታወላውሉ ትኖራላችሁ? እንግዲህ እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱን አምልኩ! ወይም ባዓል እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱኑ አምልኩ!” አላቸው፤ ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሱም። ከዚህ በኋላ ኤልያስ እንዲህ አለ፦ “ከእግዚአብሔር ነቢያት የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አራት መቶ ኀምሳ የባዓል ነቢያት ግን እነሆ በዚህ አሉ፤ እንግዲህ ሁለት ኰርማዎችን አምጡና የባዓል ነቢያት አንዱን ወስደው ይረዱት፤ ሥጋውንም ቈራርጠው እንጨት በመረብረብ በዚያ ላይ ያኑሩት፤ ነገር ግን በእሳት አያቀጣጥሉት፤ እኔም ሁለተኛውን ኰርማ ወስጄ እንደዚሁ አደርጋለሁ፤ ከዚህ በኋላ የባዓል ነቢያት ወደ አምላካቸው ይጸልዩ፤ እኔም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ እሳትን ወደ መሥዋዕቱ በመላክ መልስ የሚሰጥ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።” ሕዝቡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በዚህ ሐሳብ መስማማቱን ገለጠ። ከዚህ በኋላ ኤልያስ የባዓልን ነቢያት “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ኰርማ መርጣችሁ በማረድ ወደ አምላካችሁ ጸልዩ፤ ነገር ግን እንጨቱን በእሳት አታቀጣጥሉ” አላቸው። እነርሱም የመጣላቸውን ኰርማ ወስደው ለመሥዋዕት አዘጋጅተው እስከ እኩለ ቀን ድረስ ወደ ባዓል ጸለዩ። “ባዓል ሆይ! እባክህ ስማን!” እያሉም ጮኹ። በሠሩትም መሠዊያ እየዘለሉ ዞሩ፤ ነገር ግን ምንም መልስ አላገኙም። እኩለ ቀን ሲሆን ኤልያስ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጸልዩ! እርሱ አምላክ አይደለም እንዴ እርሱ በሐሳብ ተውጦ ይሆናል! ወይም ራሱን ያዝናና ይሆናል! ወይም ወደ ሩቅ አገር ሄዶ ይሆናል! ወይም ተኝቶ ያንቀላፋ ይሆናልና እንዲነቃ ቀስቅሱት!” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር፤ ስለዚህም የሐሰት ነቢያቱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየጸለዩ በሥርዓታቸው መሠረት ደማቸው እስኪፈስ ድረስ በቢላዋና በጩቤ ሰውነታቸውን ያቈስሉ ነበር። እኩለ ቀን ካለፈም በኋላ የሠርክ መሥዋዕት እስከሚቀርብበት ጊዜ ድረስ እየተራወጡ ይቀባጥሩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ምንም መልስ አላገኙም፤ ድምፅም አልተሰማም። ከዚህ በኋላ ኤልያስ ሰዎቹን “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ በማደስ ሠራው። እግዚአብሔር ከዚያ በፊት “እስራኤል” ብሎ ከሰየመው ከያዕቆብ በተወለዱት በዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ወሰደ፤ እነዚህንም ድንጋዮች ረብርቦ በእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በዙሪያውም ዐሥራ አራት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጒድጓድ ማሰ፤ እንጨቱንም በመሠዊያው ላይ በመረብረብ ኰርማውን በብልት በብልቱ ቈራርጦ በእንጨቱ ላይ ካኖረ በኋላ፥ “በአራት ጋን ውሃ ሞልታችሁ በመሥዋዕቱና በእንጨቱ ላይ አፍስሱት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ “አሁንም ጨምሩበት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ እርሱም “አሁንም እንደገና አንድ ጊዜ ጨምሩ!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጒድጓዱንም ሞላው። ከቀትር በኋላ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ሰዓት ነቢዩ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀርቦ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንክን፥ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን፥ እኔም ይህን ሁሉ ያደረግኹት በቃልህ መሠረት መሆኑን አንተ ራስህ ግለጥ፤ አምላኬ ሆይ! ይህ ሕዝብ አንተ እውነተኛ አምላክ መሆንህንና ወደ አንተም ያቀረብከው አንተ ራስህ መሆንህን እንዲያውቅ እባክህ መልስ ስጠኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ስማኝ!” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እሳትን ላከ፤ ያም እሳት መሥዋዕቱን፥ እንጨቱንና ድንጋዩን አቃጠለ፤ ምድሩንም ለበለበ፤ በጒድጓዱ የነበረውንም ውሃ አደረቀ፤ ሰዎቹም ይህን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው በመደነቅ “እግዚአብሔር አምላክ ነው! እውነተኛ አምላክ እርሱ ብቻ ነው!” አሉ። ኤልያስም “የባዓልን ነቢያት ያዙ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ!” ሲል አዘዘ። ሕዝቡም በሙሉ ያዛቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሾን ወንዝ እየመራ ወስዶ በዚያ ሁሉንም ገደላቸው።