ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ እስራኤልን አላወክሁም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ። አሁንም ሕዝቡ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲገናኘኝ ለመላው እስራኤል ጥሪ አድርግ። ከኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ አምሳውን የበኣል ነቢያት፣ አራት መቶውንም የአሼራ ነቢያት አምጣቸው።” ስለዚህ አክዓብ በመላው እስራኤል ጥሪ አደረገ፣ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ። ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ። ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም። ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፤ “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍሁ እኔ ብቻ ነኝ፤ በኣል ግን አራት መቶ አምሳ ነቢያት አሉት። ሁለት ወይፈኖች ስጡን፤ እነርሱም አንዱን መርጠው ይውሰዱ፤ በየብልቱም ቈራርጠው፣ በዕንጨት ላይ ያኑሩት፤ ግን እሳት አያንድዱበት፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፤ በዕንጨትም ላይ አኖረዋለሁ፤ እሳት አላነድድበትም። ከዚያ እናንተ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶ በእሳት የሚመልሰውም እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።” ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “ያልኸው መልካም ነው” አሉ። ኤልያስም ለበኣል ነቢያት፣ “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ፤ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ነገር ግን እሳት አታንድዱበት” አላቸው። ስለዚህ የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁት። ከዚያም ከጧት እስከ እኩለ ቀን የበኣልን ስም ጠሩ፤ “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ ጮኹ፤ ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም፤ በሠሩት መሠዊያ ዙሪያም እየዘለሉ ያሸበሽቡ ነበር። እኩለ ቀንም ላይ ኤልያስ፣ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ፤ አምላክ አይደለም እንዴ! ምናልባት በዐሳብ ተውጦ ወይም ሥራ በዝቶበት፣ አልያም በጕዞ ላይ ይሆናል፤ ተኝቶም ከሆነ ቀስቅሱት” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር። ስለዚህ እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ያቈስሉ ነበር። እኩለ ቀን ዐለፈ፤ እነርሱም የሠርክ መሥዋዕት እስኪቀርብ ድረስ የሚዘላብድ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም። ከዚያም ኤልያስ ሕዝቡን በሙሉ፣ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ። ከዚያም ኤልያስ፣ “ስምህ እስራኤል ይባላል” ተብሎ የእግዚአብሔር ቃል በመጣለት በያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ ወስዶ፤ በድንጋዮቹም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ዐሥራ አምስት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ዕንጨቱን ረበረበ፤ የወይፈኑንም ሥጋ በየብልቱ ከቈረጠ በኋላ፣ በዕንጨቱ ላይ አኖረው። ከዚያም፣ “ውሃ በአራት ጋን ሞልታችሁ፣ በመሥዋዕቱና በዕንጨቱ ላይ አፍስሱ” አላቸው። ደግሞም፣ “እንደ ገና ጨምሩበት” አላቸው፤ እነርሱም ጨመሩበት። “ሦስተኛም ጨምሩበት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ለሦስተኛ ጊዜ ጨመሩበት። ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጕድጓዱንም ሞላው። የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበትም ጊዜ፣ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀረብ ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና ይህን ሁሉ በትእዛዝህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይታወቅ። ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ።” ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጕድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ፣ በግንባራቸው ተደፍተው፣ “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” አሉ። ከዚያም ኤልያስ፣ “የበኣልን ነቢያት ያዟቸው! አንድም ሰው እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ፤ ሕዝቡም ያዟቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ አውርዶ አሳረዳቸው።
1 ነገሥት 18 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ነገሥት 18
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ነገሥት 18:18-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos