አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 12
12
በሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ የእስራኤል ነገዶች ማመፅ
(2ዜ.መ. 10፥1-19)
1ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ፤ በዚያም እርሱን ለማንገሥ የፈለጉ በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ እስራኤላውያን ተሰብስበው ይጠብቁት ነበር። 2ከንጉሥ ሰሎሞን በመሸሽ ወደ ግብጽ ኮብልሎ በዚያው በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ተመልሶ መጣ፤ 3እርሱንም በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ ነገዶች መልእክት ልከው አስጠሩት፤ ከእርሱም ጋር አብረው ወደ ሮብዓም በመቅረብ፥ 4“አባትህ ሰሎሞን በእኛ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖ አስጨንቆን ነበር፤ አሁን ይህን ከባድ ሸክም ብታቃልልልንና ኑሮአችንን ብታሻሽልልን እኛ ለአንተ እንገዛልሃለን” አሉት።
5ሮብዓምም “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ ሕዝቡ ሄዱ።
6ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የአባቱ የሰሎሞን አማካሪዎች የነበሩትን ሽማግሌዎች በአንድነት ሰብስቦ “እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ መልስ መስጠት እንድችል ምን ትመክሩኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
7ሽማግሌዎቹም “ዛሬ ለእነዚህ ሰዎች ታዛዥ ሆነህ ብታገለግላቸውና ለጥያቄአቸውም ተስማሚ የሆነ መልስ ብትሰጣቸው፥ እነርሱም ዘወትር በታማኝነት ያገለግሉሃል” ሲሉ መለሱለት።
8ሮብዓም ግን የሽማግሌዎቹን ምክር ቸል በማለት አብሮ ዐደጎቹ ወደነበሩት፥ አሁን ደግሞ አማካሪዎቹ ወደሆኑት ወጣቶች ዘንድ ሄዶ፤ 9“ላደርገው ስለሚገባኝ ነገር ምን ትመክሩኛላችሁ? የአገዛዝ ቀንበር እንዳቀልላቸው ለጠየቁኝስ ሰዎች ምን መልስ ልስጣቸው?” ሲል ጠየቃቸው።
10እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንተ የምትሰጣቸው መልስ ይህ ነው፤ ‘የእኔ ታናሽ ጣት ከአባቴ ወገብ ይበልጥ ትወፍራለች! 11አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ ይኸውም አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!’ ”
12ከሦስት ቀን በኋላ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ ሮብዓም በሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ተመልሰው ወደ እርሱ መጡ፤ 13ንጉሥ ሮብዓምም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ውድቅ አድርጎ ሕዝቡን በማመናጨቅ መናገር ጀመረ፤ 14ወጣቶቹም በሰጡት ምክር መሠረት “አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!” ሲል መለሰላቸው። 15ይህም የሆነበት ምክንያት ከሴሎ በመጣው በነቢዩ አኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም እግዚአብሔር የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ንጉሥ ሮብዓምም የሕዝቡን ሐሳብ ችላ በማለት ሳይቀበል የቀረበትም ምክንያት እግዚአብሔር ይህን ለውጥ ለማድረግ ስለ ወሰነ ነው።
16ሕዝቡ፥ ንጉሥ ሮብዓም ጥያቄውን እንዳልተቀበለው በተገነዘበ ጊዜ “ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅ ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደየቤትህ ሂድ! ዳዊት ሆይ የራስህን ቤት ጠብቅ!” ብለው መለሱለት። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ወደየቤቱ ሄደ። #2ሳሙ. 20፥1።
17ሮብዓምም በይሁዳ ግዛት በሚኖሩት ሕዝብ ላይ ብቻ ነገሠ።
18ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የግዳጅ ሥራ ኀላፊ የነበረውን አዶኒራምን ወደ እስራኤላውያን እንዲሄድ ላከው፤ እነርሱ ግን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህን ጊዜ ሮብዓም በፍጥነት ወደ ሠረገላው ገብቶ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ አመለጠ። 19ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ሰሜናዊ ክፍል እስራኤል በሚል ስም በዳዊት ሥርወ መንግሥት ላይ ዐመፀ።
20እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመልሶ መምጣቱን በመገንዘብ ወደ ጉባኤአቸው ጠርተው በእስራኤል ላይ አነገሡት፤ ለዳዊት ትውልዶች ታማኝ ሆኖ የቀረም የይሁዳ ነገድ ብቻ ነበር።
ሸማዕያ የተናገረው የትንቢት ቃል
(2ዜ.መ. 11፥1-4)
21ሮብዓም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከይሁዳና ከብንያም ነገዶች ተውጣጥተው የተመለሱ አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ምርጥ ወታደሮች ጠርቶ በአንድነት ሰበሰበ፤ ይህንንም ያደረገው የእስራኤልን ነገዶች ወግቶ ግዛቱን እንደገና በቊጥጥሩ ሥር ለማድረግ ዐቅዶ ስለ ነበር ነው። 22ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማዕያ መጣ፥ 23ለሮብዓም እንዲሁም ለመላው የይሁዳና የብንያም ነገዶች፥ ለቀሩትም ሰዎች ሁሉ 24“ወንድሞቻችሁ በሆኑት በእስራኤላውያን ላይ አደጋ አትጣሉ፤ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ ሂዱ፤ ይህ የሆነው በእኔ ፈቃድ ነው” ብሎ እንዲነግር አዘዘው። እነርሱም ሁሉ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዦች በመሆን ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ።
ኢዮርብዓም ፊቱን ከእግዚአብሔር ወደ ሌላ መመለሱ
25የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የምትገኘውን የሴኬምን ከተማ ምሽግ አድርጎ በዚያ ለጥቂት ጊዜ ቈየ፤ ከዚያም በመነሣት የፐኑኤልን ከተማ ምሽግ አድርጎ ሠራ፤ 26-27በሐሳቡም “ይህ ሁሉ ነገር እንዲህ ሆኖ ሳለ፥ የእኔ ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ በቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረባቸው የሚቀጥል ከሆነ፥ ለይሁዳ ንጉሥ ለሮብዓም ታማኞች በመሆን ወደ እርሱ ዞረው እኔን ይገድሉኛል፤ መንግሥቱም ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል” አለ።
28በዚህም ጉዳይ ከመከረበት በኋላ የሁለት ጥጆችን ምስል ከወርቅ አሠርቶ ለሕዝቡ “ከዚህ በፊት ታደርጉት በነበረው ዐይነት ለመስገድ እስከ ኢየሩሳሌም መሄድ ይበቃችኋል፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነሆ እነዚህ ናቸው!” አለ። #ዘፀ. 32፥4። 29ከዚህም በኋላ ከወርቅ የተሠሩት ሁለት የኰርማ ምስሎች አንዱን በቤትኤል፥ ሁለተኛውንም በዳን አቆመ፤ 30ሰዎቹም እስከ ዳን ድረስ በጣዖቱ ፊት ተሰልፈው ሄዱ፤ በዚህም ሁኔታ ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት ሠሩ፤ 31እንዲሁም ኢዮርብዓም በኮረብታዎች ላይ የማምለኪያ ስፍራዎችን አዘጋጅቶ የሌዊ ነገድ ካልሆኑ ቤተሰቦች መካከል ማንኛውንም ሰው ካህን አድርጎ ሾመ።
በቤትኤል የተጀመረው የጣዖት አምልኮ መወገዝ
32ኢዮርብዓም በይሁዳ በሚደረገው በዓል ዐይነት ስምንተኛ ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን የባዕድ አምልኮ በዓል እንዲደረግ ወሰነ፤ ከወርቅ ላሠራቸውም ምስሎች በቤትኤል በሚገኘው መሠዊያ ላይ ለጥጃ ምስሉ መሥዋዕት አቀረበ፤ በዚያም በቤትኤል ለማምለኪያ ባሠራቸው ስፍራዎች የሚያገለግሉ ካህናትን መደበ፤ 33በዓል እንዲሆን እርሱ ራሱ በወሰነው ስምንተኛ ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን ወደ ቤትኤል ሄደ፤ በዚያም ለእስራኤል በወሰነላቸው መሠረት በዓል ለማክበር በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት አቀረበ። #ዘሌ. 23፥33-34።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 12: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997