የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9

9
የሐዋርያነት መብት
1እኔ ነጻነት ያለኝ ሰው አይደለሁምን? እኔ ሐዋርያ አይደለሁምን? እኔ ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ የሥራዬ ውጤት አይደላችሁምን? 2በጌታ የሐዋርያነቴ ማረጋገጫ ማኅተም እናንተ ስለ ሆናችሁ ለሌሎቹ እንኳ ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተ ግን በእርግጥ ሐዋርያ ነኝ።
3“የሐዋርያነት መብት የለህም” ብለው የሚተቹኝ ቢኖሩ የምሰጠው መልስ ይህ ነው፤ 4እኛ ምግብና መጠጥ የማግኘት መብት የለንምን? 5እንደ ሌሎች ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ጴጥሮስም ክርስቲያን ሚስት አስከትለን የመዘዋወር መብት የለንምን? 6ወይስ በሥራ እየጣርን መኖር የሚገባን በርናባስና እኔ ብቻ ነንን? 7ያለ ደመወዝ በራሱ ገንዘብ በወታደርነት የሚያገለግል ማነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላስ ማነው? መንጋ እየጠበቀ የመንጋውን ወተት የማይጠጣ ማን ነው?
8ይህን የምናገረው በሰው አስተሳሰብ ብቻ ነውን? ሕግስ እንዲህ ይል የለምን? 9“የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ በሕግ ተጽፎአል፤ ታዲያ እግዚአብሔር ይህን ያለው ስለ በሬዎች በማሰብ ነውን? #ዘዳ. 25፥4፤ 1ጢሞ. 5፥18። 10እግዚአብሔር ይህን ያለው ስለ እኛ በማሰብ አይደለምን? የሚያርስ ገበሬ በተስፋ እንዲያርስ፥ የሚያበራይም በተስፋ እንዲያበራይ፥ በዚህ ዐይነት ሁሉም ድርሻውን እንዲያገኝ ይህ የተጻፈው በእርግጥ ስለ እኛ ነው። 11እኛ መንፈሳዊውን ነገር የዘራንላችሁ ከሆነ የእናንተን ሥጋዊ በረከት ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነውን? #ሮም 15፥27። 12ሌሎች ይህን ነገር ከእናንተ የመካፈል መብት ያላቸው ከሆነ ታዲያ፥ እኛ ከዚህ የሚበልጥ መብት እንዴት አይኖረንም? እኛ ግን በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ይህን ማድረጋችንም የክርስቶስ የምሥራች ቃል ከመስፋፋት እንዳይገታ በማሰብ ሁሉን ነገር ታግሠን እንቻል ብለን ነው። 13በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙና በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት የሚያቀርቡና የሚያገለግሉ ከመሥዋዕት ተካፍለው እንደሚበሉ ታውቁ የለምን? #ዘዳ. 18፥1። 14እንዲሁም ደግሞ ወንጌልን የሚያስተምሩ ቀለባቸውን ከዚሁ ሥራቸው እንዲያገኙ ጌታ ደንግጎአል። #ማቴ. 10፥10፤ ሉቃ. 10፥7።
15እኔ ግን በእነዚህ መብቶች በአንዱም አልተጠቀምኩም፤ ይህንንም የጻፍኩት ይህ መብቴ ሳይከበርልኝ ለምን ቀረ? በማለት አይደለም። ሰው ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ይልቅ ብሞት ይሻለኛል። 16ወንጌልን ማስተማር ግዴታዬ ስለ ሆነ የምመካበት ነገር አይደለም፤ እንዲያውም ወንጌልን ሳላስተምር ብቀር ወዮልኝ! 17የወንጌልን ቃል ያለ ግዴታ በፈቃዴ ባበሥር የድካም ዋጋ ይኖረኛል፤ በግዴታ ባደርገው ግን በዐደራ የተሰጠኝን ኀላፊነት ፈጸምኩ እንጂ ሌላ ያደረግኹት ነገር አለ ማለት አይደለም። 18ታዲያ፥ የድካሜ ዋጋ ምንድን ነው? እንግዲህ የድካሜ ዋጋ ወንጌልን በማስተማሬ ያለኝን መብት ሳልጠቀምበት ወንጌልን የማስተማር ሥራዬን ያለ ደመወዝ በነጻ መፈጸም ነው።
19እኔ የማንም ባሪያ ሳልሆን ነጻ ሰው ነኝ፤ ይሁን እንጂ በተቻለኝ መጠን ብዙዎቹን በማዳን ለመጥቀም ብዬ የሁሉም ባሪያ ሆኜአለሁ። 20ከአይሁድ ጋር ስሆን አይሁድን ለማዳን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ፤ እኔ ከሕግ በታች ባልሆንም እንኳ ከሕግ በታች ያሉትን ለማዳን ስል ከሕግ በታች እንዳሉት ሰዎች ሆንኩ። 21እኔ የእግዚአብሔር ሕግ ያለኝና ከክርስቶስ ሕግ ሥር ብሆንም እንኳ ሕግ የሌላቸውን አሕዛብ ለማዳን ስል ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንኩ። 22በእምነት ደካሞች የሆኑትን ለማዳን ስል እንደ ደካሞች ደካማ ሆንኩ፤ በተቻለ መጠን ጥቂቶችን ለማዳን ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንኩ።
23ይህን ሁሉ ማድረጌ የወንጌልን በረከት ለመካፈል ስለ ወንጌል ብዬ ነው። 24በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡና ከእነርሱም አንዱ ብቻ ሽልማት እንደሚቀበል ታውቁ የለምን? ስለዚህ እናንተም ሽልማትን ለመቀበል ሩጡ። 25በሩጫ የሚወዳደሩ ሁሉ አድካሚ ልምምድ ያደርጋሉ፤ እነርሱ እንዲህ የሚደክሙት የሚጠፋውንና ጊዜያዊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ነው፤ እኛ ግን የምንደክመው የማይጠፋውንና ዘለዓለማዊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ነው። 26እኔ ግን ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ነፋስን በቡጢ እንደሚመታ ሰው በከንቱ የምሰነዝር ሰው አይደለሁም። 27ስለዚህ ሌሎችን ወደ ውድድር ከጠራሁ በኋላ እኔ ራሴ ከውድድሩ ውጪ ሆኜ እንዳልገኝ ሰውነቴን እየተቈጣጠርኩ እንዲታዘዝልኝ አደርገዋለሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ