እያንዳንዱ ጌታ በሰጠው ስጦታና እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሰጠሁት መመሪያ ይህንኑ ነው። ማንም ሰው ከተገረዘ በኋላ የተጠራ ከሆነ እንዳልተገረዘ ለመሆን አያስብ፤ ሳይገረዝ የተጠራ ከሆነም መገረዝን አይፈልግ። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ዋጋ የለውም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር። እግዚአብሔር በጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርክን? ብትሆንም ግድ የለም፤ አትጨነቅበት፤ ነጻ የመውጣት ዕድል ብታገኝ ግን ይህ ዕድል አያምልጥህ። ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ ሰው በጌታ ነጻነትን አግኝቶአል፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ ሳለ የተጠራ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። እግዚአብሔር በዋጋ ስለ ገዛችሁ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ጊዜ በነበረበት ሁኔታ በእግዚአብሔር ጋር በዚያ ይኑር። ስላላገቡ ሰዎች ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት እምነት የሚጣልብኝ እንደ መሆኔ መጠን የራሴ ሐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው፤ አሁን ያለንበት ጊዜ የችግር ጊዜ ስለ ሆነ ሳያገቡ በብቸኝነት መኖር መልካም ይመስለኛል፤ ሆኖም ሚስት አግብተህ እንደ ሆነ ለመፍታት አትፈልግ፤ ሚስት አላገባህ እንደ ሆነ ለማግባት አትፈልግ። ነገር ግን አንተ ሚስት ብታገባ ኃጢአት ይሆንብሃል ማለት አይደለም፤ እንዲሁም አንዲት ልጃገረድ ባል ብታገባ ኃጢአት ይሆንባታል ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ የኑሮ ችግር ይገጥማቸዋል፤ የእኔም ምኞት ከዚህ ችግር እንድትድኑ ነው። ወንድሞች ሆይ! እኔ የምላችሁ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ አጥሮአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያለችው ሚስት እንደሌለችው ሆኖ ይኑሩ። ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌሉአቸው ሆነው ይኑር። የሚያዝኑም እንደማያዝኑ፥ የሚደሰቱ እንደማይደሰቱ ሆነው ይኑሩ፤ ዕቃ የሚገዙ፥ ምንም ዕቃ እንደሌላቸው አድርገው ይቊጠሩ። በዚህ ዓለም ሀብት የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ሆነው ይኑሩ፤ የአሁኑ ዓለም ሁኔታ አላፊ ነው። ስለዚህ በምንም ሐሳብ ሳትጨነቁ እንድትኖሩ እወዳለሁ፤ ሚስት ያላገባ ሰው ጌታ የሚደሰትበትን ነገር ስለሚፈልግ አሳቡ የሚያተኲረው፥ ጌታን በሚመለከት ሥራ ላይ ነው። ሚስት ያገባ ሰው ግን የሚያስበው ስለዚህ ዓለም ነገርና ሚስቱንም የሚያስደስትበትን ነገር ነው። በዚህ ሁኔታ ሐሳቡ በሁለት ተከፍሎአል ማለት ነው። እንዲሁም ባል ያላገባች ሴት ወይም ልጃገረድ በሥጋዋና በነፍስዋ ተቀድሳ የጌታ ለመሆን ስለምትፈልግ ሐሳቧ የሚያተኲረው ጌታን በሚመለከት ሥራ ነው። ያገባች ሴት ግን ባልዋን ለማስደሰት ስለምትፈልግ የምታስበው የዓለምን ነገር ነው። እኔ ይህን የምላችሁ በወጥመድ ውስጥ ገብታችሁ እንድትቸገሩ ብዬ ሳይሆን እንድትጠቀሙ ብዬ ነው፤ ምኞቴም እናንተ በተገቢው ሁኔታ እንድትኖሩና አሳባችሁ ሳይባክን በሙሉ ልባችሁ ጌታን እንድታገለግሉ ነው። አንድ ሰው እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ በኋላ ይህን ማድረጉ ለልጅትዋ መልካም ያላደረገ መሆኑ ቢሰማው፥ ከዚህም ሌላ እርስዋን ለማግባት ያለው ፍላጎት ጠንካራ ቢሆንና መጋባታቸውም ትክክል ከመሰለው እንደ ተመኘው ቢያገባት ኃጢአት አይሆንበትም፤ ስለዚህም ይጋቡ። ነገር ግን አንድ ሰው በልቡ ከጸና፥ አስገዳጅ ነገር ከሌለበት፥ ፍላጎቱን ለመቈጣጠር ከቻለና እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ መልካም አደረገ። ስለዚህ ሚስት የሚያገባ መልካም ያደርጋል፤ የማያገባ ግን የተሻለ ያደርጋል።
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:17-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች