1 ቆሮንቶስ 7:17-38

1 ቆሮንቶስ 7:17-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ነገር ግን ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ አደ​ለው፥ ሁሉም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ጠራው እን​ዲሁ ይኑር፤ ለአ​ብ​ያተ ክር​ስ​ቲ​ያ​ና​ትም ሁሉ እን​ዲህ ሥር​ዐት እን​ሠ​ራ​ለን። ተገ​ዝሮ ሳለ የተ​ጠራ ቢኖር አለ​መ​ገ​ዘ​ርን አይ​መኝ፤ ያል​ተ​ገ​ዘ​ረም ቢጠራ ከዚያ ወዲያ አይ​ገ​ዘር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ትእ​ዛዝ መጠ​በቅ ነው እንጂ መገ​ዘ​ርም አይ​ጠ​ቅ​ምም፤ አለ​መ​ገ​ዘ​ርም አይ​ጎ​ዳም። ሁሉ እንደ ተጠራ እን​ዲሁ ይኑር። አንተ ባርያ ሳለህ ብታ​ምን አያ​ሳ​ዝ​ንህ፤ የሚ​ቻ​ልህ ከሆነ ግን ነጻ​ነ​ት​ህን አግኝ። የተ​ጠራ ባሪያ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ነጻ​ነት ያለው ነውና፤ እን​ዲሁ ነጻ​ነት ያለ​ውም ከተ​ጠራ የክ​ር​ስ​ቶስ ባርያ ነው። በዋጋ ገዝ​ቶ​አ​ች​ኋ​ልና የሰው ተገ​ዦች አት​ሁኑ። ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሁላ​ች​ሁም በተ​ጠ​ራ​ች​ሁ​በት እን​ዲሁ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ኑሩ። ስለ ደና​ግ​ልም የም​ነ​ግ​ራ​ችሁ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትእ​ዛዝ አይ​ደ​ለም፤ ታማኝ እን​ድ​ሆን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይቅር ያለኝ እንደ መሆኔ ምክ​ሬን እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ እንጂ። ነገር ግን እን​ዲህ ይመ​ስ​ለ​ኛል፤ በግድ ይህ ሊመ​ረጥ ይሻ​ላ​ልና እን​ዲህ ሆኖ ቢኖር ለሰው ይሻ​ለ​ዋል። ከሚ​ስ​ትህ ጋር ሳለህ ከእ​ር​ስዋ መፋ​ታ​ትን አትሻ፤ ሚስት ከሌ​ለህ ግን ሚስ​ትን አትሻ። ብታ​ገ​ባም ኀጢ​አት አይ​ሆ​ን​ብ​ህም፤ ድን​ግ​ሊ​ቱም ባል ብታ​ገባ ኀጢ​አት አይ​ሆ​ን​ባ​ትም፤ ያገቡ ግን ለራ​ሳ​ቸው ድካ​ምን ይሻሉ፤ እኔም ይህን የም​ላ​ችሁ ስለ​ማ​ዝ​ን​ላ​ችሁ ነው። ነገር ግን ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን እን​ዲህ ይቀ​ናል፤ የዚህ ዓለም ኑሮ ሁሉ ሊያ​ልፍ ቀር​ቦ​አ​ልና፤ አሁ​ንም ያገቡ እን​ዳ​ላ​ገቡ ይሆ​ናሉ። ያለ​ቀሱ እን​ዳ​ላ​ለ​ቀሱ ይሆ​ናሉ፤ ደስ ያላ​ቸ​ውም ደስ እን​ዳ​ላ​ላ​ቸው ይሆ​ናሉ፤ የሸ​ጡም እን​ዳ​ል​ሸጡ ይሆ​ናሉ፤ የገ​ዙም እን​ዳ​ል​ገዙ ይሆ​ናሉ። የበሉ እን​ዳ​ል​በሉ ይሆ​ናሉ፤ የጠ​ጡም እን​ዳ​ል​ጠጡ ይሆ​ናሉ፤ የዚህ ዓለም ተድላ ሁሉ ያል​ፋ​ልና። እኔስ ያለ አሳብ ልት​ኖሩ እወ​ዳ​ለሁ፤ ያላ​ገባ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ደስ ሊያ​ሰ​ኘው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ነገር ያስ​ባ​ልና። ያገባ ግን ሚስ​ቱን ደስ ሊያ​ሰኝ የዚ​ህን ዓለም ኑሮ ያስ​ባል። እን​ዲህ ከሆነ ግን ተለ​ያየ፤ አግ​ብታ የፈ​ታች ሴትም ያላ​ገ​ባች ድን​ግ​ልም ብት​ሆን ነፍ​ስ​ዋም ሥጋ​ዋም ይቀ​ደስ ዘንድ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታስ​በ​ዋ​ለች፤ ያገ​ባች ግን ባል​ዋን ደስ ልታ​ሰኝ የዚ​ህን ዓለም ኑሮ ታስ​ባ​ለች። ይህ​ንም የም​ላ​ችሁ እን​ዲ​ጠ​ቅ​ማ​ችሁ ነው፤ ላጠ​ም​ዳ​ችሁ ግን አይ​ደ​ለም፤ ኑሮ​አ​ችሁ አንድ ወገን እን​ዲ​ሆ​ንና እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ያለ​መ​ጠ​ራ​ጠር እን​ድ​ታ​ገ​ለ​ግ​ሉት ነው እንጂ። በሸ​መ​ገለ ጊዜ ስለ ድን​ግ​ል​ናው እን​ደ​ሚ​ያ​ፍር የሚ​ያ​ስብ ሰው ቢኖር እን​ዲህ ሊሆን ይገ​ባል፤ የወ​ደ​ደ​ውን ያድ​ርግ፤ ቢያ​ገ​ባም ኀጢ​አት የለ​በ​ትም። በልቡ የቈ​ረ​ጠና ያላ​ወ​ላ​ወለ ግን የወ​ደ​ደ​ውን ሊያ​ደ​ርግ ይች​ላል፤ ግድም አይ​በ​ሉት፤ ድን​ግ​ል​ና​ው​ንም ይጠ​ብቅ ዘንድ በልቡ ቢጸና መል​ካም አደ​ረገ። ድን​ግ​ሊ​ቱን ያገባ መል​ካም አደ​ረገ፤ ያላ​ገባ ግን የም​ት​ሻ​ለ​ውን አደ​ረገ።

1 ቆሮንቶስ 7:17-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ብቻ እያንዳንዱ ሰው ጌታ እንደ ወሰነለት፣ እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው በዚያው ይመላለስ። በአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ የምንደነግገው ይህንኑ ነው። አንድ ሰው ተገርዞ ሳለ ቢጠራ፣ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን፤ ሳይገረዝም ተጠርቶ ከሆነ አይገረዝ። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸሙ ነው። እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ጸንቶ ይኑር። በተጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርህን? በዚህ አትጨነቅ፤ ነጻነትህን ማግኘት ከቻልህ ግን ነጻነትህን ተቀበል። ምክንያቱም ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ፣ የጌታ ነጻ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ ስለዚህ የሰው ባሮች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ፤ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋራ ጸንቶ ይኑር። ስለ ደናግል፣ ከጌታ የተቀበልሁት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ምሕረት የተነሣ እንደ ታማኝ ሰው፣ ምክሬን እሰጣለሁ። አሁን ካለው ችግር የተነሣ ባላችሁበት ሁኔታ ብትኖሩ መልካም ይመስለኛል። አግብተህ ከሆነ መፋታትን አትሻ፤ ካላገባህም ሚስት ለማግባት አትፈልግ። ብታገባ ግን ኀጢአት አልሠራህም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኀጢአት አላደረገችም። ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፤ እኔም ይህ እንዳይደርስባችሁ እወድዳለሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ሐሳቤ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ ዐጭር ነው፤ ከእንግዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ይኑሩ። የሚያለቅሱ እንደማያለቅሱ፣ ደስተኞች ደስ እንደማይላቸው ይሁኑ፤ ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቍጠሩ፤ በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም መልክ ዐላፊ ነውና። እኔስ ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወድዳለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሠኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል፤ ያገባ ሰው ግን ሚስቱን ደስ ለማሠኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤ በዚህም ልቡ ተከፍሏል። ያላገባች ሴት ወይም ድንግል ስለ ጌታ ነገር ታስባለች፤ ዐላማዋም በሥጋና በመንፈስ ለጌታ መቀደስ ነው። ያገባች ሴት ግን ባሏን ደስ ለማሠኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች። ይህንም የምለው ለእናንተ የሚበጃችሁን ነገር በማሰብ እንጂ ላስጨንቃችሁ አይደለም፤ ዐላማዬም ልባችሁ ሳይከፈል በጌታ ጸንታችሁ በአግባብ እንድትኖሩ ነው። አንድ ሰው ያጫትን ድንግል በአግባቡ ካልያዘ፣ እርሷም በዕድሜ እየገፋች ከሄደች፣ ሊያገባት ካሰበ የወደደውን ያድርግ፤ ኀጢአት የለበትምና ይጋቡ። ነገር ግን በዚህ ጕዳይ ልቡን አረጋግቶ፣ ሳይናወጥ፣ ራሱንም በመግዛት ድንግሊቱን ላለማግባት የወሰነ ሰው መልካም አድርጓል። ስለዚህ ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባም የተሻለ አደረገ።

1 ቆሮንቶስ 7:17-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ። መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ከንቱ ነው፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር። ባሪያ ሆነህ ተጠርተህ እንደ ሆነ አይገድህም፤ አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል። ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር። ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ። እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር። ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል። ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም። ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ። ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ። እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።

1 ቆሮንቶስ 7:17-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እያንዳንዱ ጌታ በሰጠው ስጦታና እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሰጠሁት መመሪያ ይህንኑ ነው። ማንም ሰው ከተገረዘ በኋላ የተጠራ ከሆነ እንዳልተገረዘ ለመሆን አያስብ፤ ሳይገረዝ የተጠራ ከሆነም መገረዝን አይፈልግ። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ዋጋ የለውም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር። እግዚአብሔር በጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርክን? ብትሆንም ግድ የለም፤ አትጨነቅበት፤ ነጻ የመውጣት ዕድል ብታገኝ ግን ይህ ዕድል አያምልጥህ። ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ ሰው በጌታ ነጻነትን አግኝቶአል፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ ሳለ የተጠራ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። እግዚአብሔር በዋጋ ስለ ገዛችሁ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ጊዜ በነበረበት ሁኔታ በእግዚአብሔር ጋር በዚያ ይኑር። ስላላገቡ ሰዎች ከጌታ የተቀበልኩት ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት እምነት የሚጣልብኝ እንደ መሆኔ መጠን የራሴ ሐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው፤ አሁን ያለንበት ጊዜ የችግር ጊዜ ስለ ሆነ ሳያገቡ በብቸኝነት መኖር መልካም ይመስለኛል፤ ሆኖም ሚስት አግብተህ እንደ ሆነ ለመፍታት አትፈልግ፤ ሚስት አላገባህ እንደ ሆነ ለማግባት አትፈልግ። ነገር ግን አንተ ሚስት ብታገባ ኃጢአት ይሆንብሃል ማለት አይደለም፤ እንዲሁም አንዲት ልጃገረድ ባል ብታገባ ኃጢአት ይሆንባታል ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ የኑሮ ችግር ይገጥማቸዋል፤ የእኔም ምኞት ከዚህ ችግር እንድትድኑ ነው። ወንድሞች ሆይ! እኔ የምላችሁ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ አጥሮአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስት ያለችው ሚስት እንደሌለችው ሆኖ ይኑሩ። ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌሉአቸው ሆነው ይኑር። የሚያዝኑም እንደማያዝኑ፥ የሚደሰቱ እንደማይደሰቱ ሆነው ይኑሩ፤ ዕቃ የሚገዙ፥ ምንም ዕቃ እንደሌላቸው አድርገው ይቊጠሩ። በዚህ ዓለም ሀብት የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙበት ሆነው ይኑሩ፤ የአሁኑ ዓለም ሁኔታ አላፊ ነው። ስለዚህ በምንም ሐሳብ ሳትጨነቁ እንድትኖሩ እወዳለሁ፤ ሚስት ያላገባ ሰው ጌታ የሚደሰትበትን ነገር ስለሚፈልግ አሳቡ የሚያተኲረው፥ ጌታን በሚመለከት ሥራ ላይ ነው። ሚስት ያገባ ሰው ግን የሚያስበው ስለዚህ ዓለም ነገርና ሚስቱንም የሚያስደስትበትን ነገር ነው። በዚህ ሁኔታ ሐሳቡ በሁለት ተከፍሎአል ማለት ነው። እንዲሁም ባል ያላገባች ሴት ወይም ልጃገረድ በሥጋዋና በነፍስዋ ተቀድሳ የጌታ ለመሆን ስለምትፈልግ ሐሳቧ የሚያተኲረው ጌታን በሚመለከት ሥራ ነው። ያገባች ሴት ግን ባልዋን ለማስደሰት ስለምትፈልግ የምታስበው የዓለምን ነገር ነው። እኔ ይህን የምላችሁ በወጥመድ ውስጥ ገብታችሁ እንድትቸገሩ ብዬ ሳይሆን እንድትጠቀሙ ብዬ ነው፤ ምኞቴም እናንተ በተገቢው ሁኔታ እንድትኖሩና አሳባችሁ ሳይባክን በሙሉ ልባችሁ ጌታን እንድታገለግሉ ነው። አንድ ሰው እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ በኋላ ይህን ማድረጉ ለልጅትዋ መልካም ያላደረገ መሆኑ ቢሰማው፥ ከዚህም ሌላ እርስዋን ለማግባት ያለው ፍላጎት ጠንካራ ቢሆንና መጋባታቸውም ትክክል ከመሰለው እንደ ተመኘው ቢያገባት ኃጢአት አይሆንበትም፤ ስለዚህም ይጋቡ። ነገር ግን አንድ ሰው በልቡ ከጸና፥ አስገዳጅ ነገር ከሌለበት፥ ፍላጎቱን ለመቈጣጠር ከቻለና እጮኛውን ላለማግባት ከወሰነ መልካም አደረገ። ስለዚህ ሚስት የሚያገባ መልካም ያደርጋል፤ የማያገባ ግን የተሻለ ያደርጋል።

1 ቆሮንቶስ 7:17-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እያንዳንዱ ጌታ በሰጠውና እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሰጠሁት መመሪያ ይህ ነው። ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደሆነ፥ መገረዝን አይፈልግ። መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ምንም ማለት አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። እያንዳንዱ ሲጠራ በነበረበት ሁኔታ ይኑር። ባርያ ሆነህ ተጠርተህ እንደሆነ አይገድህም፤ ነጻ ልትወጣ ቢቻልህ ግን ነጻነትን ተቀበል። ባርያ ሆኖ ሳላ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ ሳለ የተጠራ የክርስቶስ ባርያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባርያዎች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ! እያንዳንዱ በተጠራ ጊዜ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር። ደናግልን በተመለከተ የጌታ ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት የታመንሁ እሆን ዘንድ ምክሬን እለግሳችሀለሁ፤ እንግዲህ አሁን ላለንበት ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ሚስት አግብተህ እንደሆንህ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት አላገባህ እንደሆንህ ለማግባት አትፈልግ። ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይገጥማቸዋል፤ እኔም ከዚያ ባስጣልኳችሁ ነበር። ዳሩ ግን ወንድሞች ሆይ! ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። ነገር ግን ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንደሚያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፤ ልቡም ተከፍሎአል። ያላገባች ሴትና ድንግል በሰውነት በመንፈስም እንድትቀደስ የጌታን ነገር ታስባለች፤ ያገባች ግን ባሏን እንዴት ደስ እንደምታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአግባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም ለጌታ በጽናት እንድታገለግሉ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም። ዳሩ ግን አንድ ሰው በእጮኛው ላይ መልካም አለማድረጉን ቢያስብ፥ እጮኛውም ዕድሜዋ ለጋብቻ ከደረሰ፥ ሊያገባም ከፈቀደ፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ። ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ምንም አስገዳጅ የለበትም፤ ፍላጎቱን ለመቆጣጠር ከቻለና እጮኛውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ። ስለዚህ ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ፥ ያላገባም የተሻለ አደረገ።