የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:12-28

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:12-28 አማ05

ነገር ግን ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ የምናስተምር ከሆነ ከእናንተ አንዳንዶቹ ከሞት መነሣት የለም እንዴት ይላሉ? ከሞት መነሣት ከሌለ ክርስቶስ ከሞት አልተነሣም ማለት ነው፤ ክርስቶስ ከሞት ካልተነሣ የእኛም ትምህርት ሆነ የእናንተም እምነት ከንቱ መሆኑ ነው፤ ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በማስተማራችን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነናል ማለት ነው፤ እንግዲህ የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ እግዚአብሔር ክርስቶስንም ከሞት አላስነሣውም ማለት ነው። የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ ክርስቶስም ከሞት አልተነሣም ማለት ነው። ክርስቶስ ከሞት ያልተነሣ ከሆነ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ ገና በኃጢአታችሁ ውስጥ ትኖራላችሁ ማለት ነው፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱት ጠፍተዋል ማለት ነው፤ በክርስቶስ ተስፋ የምናደርገው ለዚህ ዓለም ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የሚታዘንልን መሆናችን ነው፤ ነገር ግን ክርስቶስ ለሞቱት ከሞት የመነሣት በኲር ሆኖ በእርግጥ ከሞት ተነሥቶአል። ሞት የመጣው በአንዱ ሰው በአዳም ምክንያት እንደ ሆነ ከሞት መነሣትም የሚመጣው በአንዱ ሰው በክርስቶስ ምክንያት ነው። በአዳም ምክንያት ሰው ሁሉ እንደሚሞት እንዲሁም በክርስቶስ ምክንያት ሰው ሁሉ ሕይወትን ያገኛል። ይህም የሚሆነው ለእያንዳንዱ በየተራው ነው፤ ክርስቶስ ከሞት የመነሣት የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፤ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት ከሞት ይነሣሉ። ቀጥሎም እርሱ ግዛትንና ሥልጣንን ኀይልንም ሁሉ አጥፍቶ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ በሚያስረክብበት ጊዜ የዓለም ፍጻሜ ይሆናል። እግዚአብሔር ጠላቶቹን ሁሉ በሥልጣኑ ሥር እስኪያደርግለት ድረስ ክርስቶስ መንገሥ ይገባዋል። ተሸንፎ በመጨረሻ የሚደመሰሰው ጠላት ሞት ነው። “እግዚአብሔር ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር አድርጎለታል” የሚል ተጽፎአል፤ ነገር ግን “ሁሉ ነገር በሥልጣኑ ሥር ሆኖአል” ሲባል ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር ያደረገለትን እግዚአብሔር አብን አይጨምርም። ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥልጣን ሥር ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር አብ ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር በአደረገለት በእግዚአብሔር አብ ሥልጣን ሥር ይሆናል።