የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14:1-12

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14:1-12 አማ05

እንግዲህ ፍቅርን ተከታተሉ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ይልቁንም ትንቢት የመናገር ስጦታን በብርቱ ፈልጉ። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ ምሥጢር የሆነውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ስለሚናገር የሚናገረውን ቃል የሚያውቀው የለም። ትንቢትን የሚናገር ግን ሌላውን ለማነጽ፥ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰዎች ይናገራል። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገር ሰው ራሱን ብቻ ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበረ ክርስቲያንን ያንጻል። ሁላችሁም በተለያዩ ቋንቋዎች ብትናገሩ እወድ ነበር፤ ይበልጥ የምወደው ግን ትንቢትን ብትናገሩ ነው፤ ማኅበረ ምእመናን እንዲታነጽ በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የሚተረጒም ከሌለ፥ በተለያዩ ቋንቋዎች ከሚናገር ሰው ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ሰው ይበልጣል። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተናገርኩ ብመጣ ምን እጠቅማችኋለሁ? ይልቅስ የምጠቅማችሁ የእግዚአብሔርን ምሥጢር መግለጥን፥ ዕውቀትን፥ ትንቢት መናገርን፥ ትምህርትን ይዤላችሁ ብመጣ ነው። እንደ ዋሽንትና እንደ ክራር ያሉት ነፍስ የሌላቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች እንኳ የተለየ የድምፅ ቅኝት ከሌላቸው የሚሰጡት የሙዚቃ ድምፅ ምን መሆኑ እንዴት ይታወቃል? እምቢልታ በማይታወቅ ድምፅ ቢነፋ፤ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እንዲሁም እናንተ በቋንቋ ስትነጋገሩ ግልጥ በሆኑ ቃሎች ካልተናገራችሁ የምትናገሩትን ማን ሊያውቀው ይችላል? ለነፋስ እንደምትናገሩ ትሆናላችሁ። በዓለም ላይ ብዙ ቋንቋዎች አሉ፤ ትርጒም የሌለው ቋንቋም የለም። እንግዲህ እኔ የሚነገረውን ቋንቋ ትርጒም የማላውቅ ብሆን ለተናጋሪው ሰው እንግዳ እሆናለሁ፤ እርሱም ለእኔ እንግዳ ይሆናል። እናንተም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች በብርቱ ስለምትሹ በይበልጥ መፈለግ የሚገባችሁ ክርስቲያኖች የሚታነጹባቸው ስጦታዎች እንዲበዙላችሁ ነው።