የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ቆሮንቶስ 14:1-12

1 ቆሮንቶስ 14:1-12 NASV

ፍቅርን ተከታተሉ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፣ በተለይም ትንቢት የመናገርን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርምና፤ ምስጢር የሆነውን በመንፈስ ስለሚናገር የሚረዳው የለም። ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ለሰው ይናገራል። በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል። ሁላችሁም በልሳን ብትናገሩ እወድዳለሁ፤ ከዚህ ይልቅ ግን ትንቢትን ብትናገሩ እወድዳለሁ። ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ በልሳን የሚናገር ሰው የተናገረውን ካልተረጐመ፣ በልሳን ከሚናገር ይልቅ ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ በመግለጥ ወይም በዕውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ በልሳን ብናገር ምን እጠቅማችኋለሁ? እንደ ዋሽንትና እንደ በገና ያሉ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች እንኳ፣ የድምፃቸው ቃና ልዩነት ከሌለው የዋሽንት ወይም የበገና ድምፅ መሆኑን እንዴት ማወቅ ይቻላል? ደግሞም መለከት ትክክል ያልሆነ የጥሪ ድምፅ ካሰማ፣ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ ከአንደበታችሁ ትርጕም ያለው ቃል ካልወጣ፣ የምትናገሩትን ማን ሊያስተውለው ይችላል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ። በዓለም ላይ ብዙ ዐይነት ቋንቋዎች አሉ፤ ትርጕም የሌለውም ቋንቋ የለም። እንግዲህ አንድ ሰው የሚናገረውን ቋንቋ ትርጕሙን ካላወቅሁ፣ ለሚናገረው እንግዳ እሆንበታለሁ፤ እርሱም ለእኔ እንግዳ ይሆንብኛል። እናንተም እንደዚሁ ናችሁ፤ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማግኘት የምትሹ በመሆናችሁ፣ ቤተ ክርስቲያን የምትታነጽበትን ስጦታዎች ለማግኘት ይበልጥ ፈልጉ።