የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11:1-16

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11:1-16 አማ05

እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ። ዘወትር ስለምታስታውሱኝና የሰጠኋችሁንም ትውፊት አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ፥ አመሰግናችኋለሁ። ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴት ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር አብ መሆኑን እንድታውቁ እወዳለሁ። ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። እንዲሁም ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የትንቢት ቃል የምትናገር ሴት በሴት ላይ ሥልጣን ያለውን ወንድን ታዋርዳለች፤ ራስዋን የማትከናነብ ሴት እንደ ተላጨች ትቈጠራለች። ሴት ራስዋን የማትከናነብ ከሆነ ጠጒርዋን ትቈረጥ፤ ነገር ግን ጠጒርዋን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያዋርዳት ነገር ከሆነ ራስዋን ትከናነብ። ወንድ የእግዚአብሔር መልክና የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም። እንዲሁም ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም፤ በዚህ ምክንያትና በመላእክትም ምክንያት ሴት የሥልጣን ምልክት የሆነውን መከናነቢያ በራስዋ ላይ ታድርግ። በጌታ ባለን ሕይወት ሴት ያለ ወንድ አትኖርም፤ ወንድም ያለ ሴት አይኖርም። ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች እንዲሁም ወንድ የሚወለደው ከሴት ነው፤ ነገር ግን ወንድም ሆነ ሴት ሌላውም ነገር ሁሉ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው። እስቲ ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትከናነብ ወደ እግዚአብሔር መጸለይዋ ተገቢ ነውን? ወንድ ጠጒሩን ቢያስረዝም ነውር እንደሚሆንበት ተፈጥሮ ራሱ ያስተምራችሁ የለምን? ሴት ግን ጠጒር የተሰጣት ራሷን ልትሸፍንበት ስለ ሆነ ጠጒርዋን ብታስረዝም ለእርስዋ ክብርዋ ነው። ስለዚህ ጉዳይ መከራከር የሚፈልግ ሰው ቢኖር እኛም ሆንን ወይም ሌሎች የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያን ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።