የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ቆሮንቶስ 11:1-16

1 ቆሮንቶስ 11:1-16 NASV

እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ። በሁሉም ነገር ስለምታስቡልኝና ከእኔ የተቀበላችሁትን ትምህርት አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። ነገር ግን ይህን እንድታውቁ እወድዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው። ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ወንድ የርሱን ራስ ያዋርዳል፤ ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ማንኛዋም ሴት የእርሷን ራስ ታዋርዳለች፤ ጠጕሯን እንደ ተላጨች ይቈጠራልና። ሴት ራሷን የማትሸፍን ከሆነ፣ ጠጕሯን ትቈረጥ፤ ጠጕሯን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር መስሎ ከታያት ግን ራሷን ትሸፈን። ወንድ ራሱን መከናነብ የለበትም፤ ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ነውና፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት፤ ምክንያቱም ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም። ደግሞም ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም። በዚህ ምክንያት፣ በመላእክትም ምክንያት፣ ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ። በጌታ ዘንድ ግን ሴት ያለ ወንድ፣ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች ሁሉ፣ ወንድም ከሴት ይወለዳልና፤ ነገር ግን የሁሉም መገኛ እግዚአብሔር ነው። እስኪ እናንተ ፍረዱ፤ ሴት ራሷን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይገባታልን? ወንድ ጠጕሩን ቢያስረዝም ነውር እንደሚሆንበት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? ሴት ግን ጠጕሯን ብታስረዝም ክብሯ አይደለምን? ረዥም ጠጕር የተሰጣት መጐናጸፊያ እንዲሆናት ነውና። እንግዲህ ማንም በዚህ ጕዳይ ላይ መከራከር ቢፈልግ፣ እኛም ሆንን የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።