የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 5

5
የሮቤል ትውልድ
1የያዕቆብ የበኲር ልጅ የሆነው የሮቤል ዘሮች ቀጥሎ የተመለከቱት ናቸው፤ (ሮቤል የአባቱን አልጋ ደፍሮ በማርከሱ የብኲርናውን መብት ስላጣ፥ ያ መብት ለዮሴፍ ተሰጥቶ ነበር፤ #ዘፍ. 35፥22፤ 49፥3-4። 2ይሁን እንጂ ከሁሉም ይበልጥ ብርቱ የሆነና ለነገዶች ሁሉ መሪ የሚሆን ሰው የሚገኝበት የይሁዳ ነገድ ነበር፤) #ዘፍ. 49፥8-10። 3ከያዕቆብ ልጆች በኲር የሆነው ሮቤል አራት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔጽሮንና ካርሚ ተብለው የሚጠሩት ናቸው።
4-6ከትውልድ እስከ ትውልድ የነበሩት የዮኤል ዘሮች ሸማዕያ፥ ጎግ፥ ሺምዒ፥ ሚካ፥ ረአያ፥ በዓልና፥ በኤራ ናቸው፤ የአሦራውያን ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር የጐሣ መሪ የነበረውን በኤራን ይዞ በምርኮኛነት ወሰደው። #2ነገ. 15፥29።
7የቤተሰብ ስም ዝርዝር ከሚገልጠው መዝገብ በተገኘው መሠረት የሮቤል ነገድ የጐሣ አለቆች የነበሩት ኢዩኤል፥ ዘካርያስና፥ 8ከዩኤል ጐሣ የሼማዕ የልጅ ልጅ የዓዛዝ ልጅ የሆነው ቤላዕ ናቸው፤ ይህም ጐሣ ይኖር የነበረው በዓሮዔርና ከዚያም በስተሰሜን እስከ ነቦና እስከ ባዓልመዖን ባለው ግዛት ነበር፤ 9እነርሱም በገለዓድ ምድር ብዙ የከብት መንጋ ስለ ነበራቸው በስተ ምሥራቅ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ተንጣልሎ ያለውን በረሓማ ምድር ሁሉ ያዙ። 10በንጉሥ ሳኦል ዘመነ መንግሥት የሮቤል ነገድ በሀጋራውያን ላይ አደጋ ጥሎ ሁሉንም በጦርነት ፈጃቸው፤ በገለዓድም ምሥራቃዊ ክፍል ያለውን ርስታቸውን ይዞ የራሱ አደረገ።
የጋድ ትውልድ
11የጋድ ነገድ፥ የሮቤል ነገድ ከሚኖሩበት በስተ ሰሜን ባለው ምድር ይኖሩ ነበር፤ ይህም ምድር በባሳን ውስጥ ሲሆን በስተ ምሥራቅ እስከ ሳለካ ይደርሳል። 12ኢዩኤል ከሁሉ ለሚበልጠው ጐሣ አባት ሲሆን፥ ሻፋም ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ለሚገኘው ጐሣ አባት ነው፤ ያዕናይና ሻፋጥ በበሳን ይኖሩ ለነበሩት ለሌሎች ጐሣዎች አባቶች ነበሩ፤ 13የቀሩት የዚህ ነገድ አባሎች ሚካኤል፥ መሹላም፥ ሼባዕ፥ ዮራይ፥ ያዕካን፥ ዚዓና ዔቤር ተብለው በሚጠሩ ሰባት ጐሣዎች የተጠቃለሉ ነበሩ፤ 14እነርሱም የሑሪ ልጅ የኢቢኃይል ዘሮች ሲሆኑ፥ የቀድሞ አባቶቻቸው አቢኃይል፥ ሑሪ፥ ያሮሐ፥ ገለዓድ፥ ሚካኤል፥ የሺሻይ፥ ያሕዶና ቡዝ ናቸው፤ 15የጉኒ የልጅ ልጅ የዓብዲኤል ልጅ አሒ የእነዚህ ሁሉ ጐሣዎች አለቃ ነበር፤ 16እነዚህም ሁሉ በባሳንና በገለዓድ ግዛቶች፥ በዚያም በሚገኙ ታናናሽ ከተሞች እንዲሁም በሳሮን ምድር የግጦሽ ቦታ ባለበት ስፍራ ሁሉ ይኖሩ ነበር። 17ይህ የቤተሰብን ስም ዝርዝር የያዘ መዝገብ የተዘጋጀው በይሁዳ ንጉሥ ኢዮአታምና በእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነበር።
የምሥራቅ ነገዶች ሠራዊት
18የሮቤል፥ የጋድና በስተ ምሥራቅ የሚገኘው የምናሴ ነገድ እኩሌታ በጋሻና በሰይፍ እንዲሁም በቀስት ውጊያ በደንብ የሠለጠኑ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሥልሳ ወታደሮች ነበሩአቸው፤ 19እነርሱም የሀጋራውያን ነገዶች በሆኑት በየጡር፥ በናፊሽና በኖዳብ ሕዝቦች ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። 20እምነታቸውንም በእግዚአብሔር አድርገው እርሱ እንዲረዳቸው ተማጠኑት፤ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን ሰምቶ፥ በሀጋራውያንና በእነርሱም የጦር ጓደኞች ላይ ድልን አጐናጸፋቸው፤ 21ከጠላትም እጅ ኀምሳ ሺህ ግመሎችን፥ ሁለት መቶ ኀምሳ ሺህ በጎችንና ሁለት ሺህ አህዮችን ማረኩ፤ እንዲሁም አንድ መቶ ሺህ ሰዎችን ምርኮኛ አድርገው ወሰዱ። 22ጦርነቱ እግዚአብሔር የፈቀደው ስለ ነበረ፥ ከጠላት ወገን ብዙ ሰዎችን ገደሉ፤ እነርሱም ራሳቸው ተማርከው እስከ ተወሰዱበት ጊዜ ድረስ በምድሪቱ ላይ መኖራቸውን ቀጠሉ።
በስተ ምሥራቅ ያለው የምናሴ ነገድ
23በስተ ምሥራቅ ያለው የምናሴ ነገድ እኩሌታ በስተ ሰሜን እስከ ባዓልሔርሞን፤ እስከ ሠኒርና እስከ ሔርሞን ተራራ በሚደርሰው በባሳን ግዛት ውስጥ ይኖሩ ነበር፤ የሕዝባቸውም ቊጥሩ እየበዛ ሄደ፤ 24የጐሣዎቻቸው አለቆች ዔፌር፥ ዩሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝሪኤል፥ ኤርምያስ፥ ሆዳውያና ያሕዲኤል ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የታወቁ የጐሣ መሪዎችና ጀግኖች ወታደሮች ነበሩ።
በምሥራቅ በኩል ያሉት የሁለት ተኩል ነገድ ሕዝብ ተማርከው ተወሰዱ
25ሕዝቡ ለቀድሞ አባቶቹ አምላክ ታማኝ ሆኖ አልተገኘም፤ እንዲያውም እግዚአብሔርን ትቶ ከምድሪቱ ላይ ላስወገደለት ሕዝብ አማልክት ሰገደ። 26ስለዚህ እግዚአብሔር ፑል ወይም ቲግላት ፐሌሴር ተብሎ የሚጠራውን የአሦርን ንጉሠ ነገሥት አነሣሥቶ ምድራቸውን እንዲወር አደረገ፤ በዚህ ዐይነት ቲግላት ፐሌሴር የሮቤልን፥ የጋድንና በምሥራቅ በኩል ያለውን የምናሴን ነገድ እኩሌታ ማርኮ በመውሰድ በሐላሕ፥ በሐቦርና በሃራ እንዲሁም በጎዛን ወንዝ ዳርቻ እንዲኖሩ አደረጋቸው እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው ይገኛሉ። #2ነገ. 15፥19፤29፤ 17፥6።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ