የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 6

6
የሊቀ ካህናት ቤተሰብ የትውልድ ሐረግ
1የሌዊ ልጆች እነርሱም ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፤ 2ቀዓትም ዓምራም፥ ይጽሐር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል ተብለው የሚጠሩትን ወንዶች ልጆችን ወለደ።
3ዓምራምም አሮንና ሙሴ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆችና ማርያም ተብላ የምትጠራ አንዲት ሴት ልጅ ወለደ።
አሮንም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ተብለው የሚጠሩ ወንዶች ልጆች ነበሩት።
4አልዓዛር ፊንሐስን ወለደ፤ ፊንሐስ አቢሹዓን ወለደ፤ አቢሹዓ ቡቂን ወለደ፤ 5ቡቂ ዑዚን ወለደ፤ 6ዑዚ ዘራሕያን ወለደ፤ ዘራሕያ መራዮትን ወለደ፤ 7መራዮት አማርያን ወለደ፤ አማርያ አሒጦብን ወለደ፥ 8አሒጦብ ጻዶቅን ወለደ፤ ጻዶቅ አሒማዓጽን ወለደ፤ 9አሒማዓጽ አዛርያስን ወለደ፤ ዓዛርያስም ዮሐናን ወለደ፤ 10ዮሐና ዓዛርያስን ወለደ፤ አዛርያስ ንጉሥ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ባሠራው ቤተ መቅደስ በክህነት ያገለግል የነበረ ነው። 11ዐዛርያስ አማርያን ወለደ፤ አማርያ አሒጡብን ወለደ፤ 12አሒጡብ ጻዶቅን ወለደ፤ ጻዶቅ ሻሉምን ወለድ፤ 13ሻሉም ሒልቂያን ወለደ፤ ሒልቂያ ዐዛርያስን ወለደ፤ 14ዐዛርያስ ሤራያን ወለደ፤ ሤራያም ኢዮጼዴቅን ወለደ። 15እግዚአብሔር የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በናቡከደነፆር ተማርከው በስደት እንዲኖሩ ባደረገ ጊዜ ኢዮጼዴቅም ከእነርሱ ጋር ተማርኮ ሄደ።
የሌዊ ትውልድ
16ሌዊ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ 17ጌርሾንም ሊብኒንና ሺምዒን ወለደ፤ 18ቀዓትም ዓምራምን፥ ይጽሐርን፥ ኬብሮንንና ዑዚኤልን ወለደ፤ 19መራሪ ደግሞ ማሕሊንና ሙሺን ወለደ። የሌዊ የነገድ ወገኖች በየትውልዳቸው የሚከተሉት ናቸው፦ #ዘፀ. 6፥16-19።
20ጌርሾን ሊብኒን ወለደ፤ ሊብኒ ያሐትን ወለደ፤ ያሐት ዚማን ወለደ፤ 21ዚማ ዮአሕን ወለደ፤ ዮአሕ ዒዶን ወለደ፤ ዒዶ ዜራሕን ወለደ፤ ዜራሕም የአትራይን ወለደ።
22የቀዓት ዘሮች፦ ቀዓት ዐሚናዳብን ወለደ፤ ዐሚናዳብ ቆሬን ወለደ፤ ቆሬ አሲርን ወለደ፤ 23አሲር ኤልቃናን ወለደ፤ ኤልቃና ኤቢያሳፍን ወለደ፤ ኤቢያሳፍ አሲርን ወለደ፤ 24አሲር ታሐትን ወለደ፤ ታሐት ኡሪኤልን ወለደ፤ ኡሪኤል ዑዚያን ወለደ፤ ዑዚያም ሻኡልን ወለደ።
25የኤልቃና ዘሮች ኤልቃናም ዐማሣይንና አሒሞትን ወለደ፤ 26አሒሞትም ኤልቃናን ወለደ፤ ኤልቃናም ጾፋይን ወለደ፤ ጾፋይ ናሐትን ወለደ፤ 27ናሐት ኤሊያብን ወለደ፤ ኤልያብ ይሮሐምን ወለደ፤ ይሮሐምም ሕልቃናን ወለደ።
28የሳሙኤል ልጆች፦ ሳሙኤል ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም በኲሩ ኢዩኤል ሁለተኛው አቢያ ተብለው ይጠሩ ነበር።
29የመራሪ ዘሮች፦ መራሪ ማሕሊን ወለደ፤ ማሕሊ ሊብኒን ወለደ፤ ሊብኒ ሺምዒን ወለደ ሺምዒ ዑዛን ወለደ፤ 30ዑዛ ሺምዓን ወለደ፤ ሺምዓ ሐጊያን ወለደ፤ ሐጊያም ዐሳያን ወለደ።
የቤተ መቅደስ መዘምራን
31የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት ለሚያገለግሉት መዘምራን ኀላፊ የሚሆኑ ሰዎችን ሾመ፤ 32ንጉሥ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ከመሥራቱ በፊት እግዚአብሔር በሚመለክበት ድንኳን የመዘመር ተግባራቸውን ያከናውኑ ነበር፤ የሥራቸውንም ቅደም ተከተል በተዘጋጀላቸው ተራ መሠረት ይፈጽሙ ነበር። 33በዚህ ቦታ ተመድበው የሚያገለግሉት ሰዎች የቤተሰብ የትውልድ ሐረግ እንደሚከተለው ነው፦
የቀዓት ጐሣ፦ የመጀመሪያው የመዘምራን ቡድን መሪ ኢዩኤል ልጅ ዘማሪው ሄማን ነበር፤ የእርሱም የቤተሰብ የትውልድ ሐረግ ከዚህ በታች በተመለከተው አኳኋን እስከ ያዕቆብ ይደርሳል፦ ሄማን፥ ዮኤል፥ ሳሙኤል፥ 34ሕልቃና፥ ይሮሐም፥ ኤሊኤል፥ ቶሐ፥ 35ጹፍ፥ ኤልቃና፥ ማሐት፥ ዐማሣይ፥ 36ኤልቃና፥ ኢዩኤል፥ ዐዛርያ፥ ሶፎንያስ፥ 37ታሐት፥ አሲር፥ ኤቢያሳፍ፥ ቆሬ፥ 38ይጽሐር፥ ቀዓት፥ ሌዊ፥ ያዕቆብ።
39በቀኙ በኩል የቆመው የሁለተኛው የመዘምራን ቡድን መሪ አሳፍ ነበር፤ የእርሱም የቤተሰብ የትውልድ ሐረግ ከዚህ በታች በተመለከተው አኳኋን እስከ ሌዊ ይደርሳል፦ አሳፍ፥ በራክያ፥ ሺምዓ፥ 40ሚካኤል፥ ባዕሴያ፥ ማልኪያ፥ 41ኤትኒ፥ ዜራሕ፥ ዐዳያ፥ 42ኤታን፥ ዚማ፥ ሺምዒ፥ 43ያሐት፥ ጌርሾን፥ ሌዊ።
44በግራው በኩል የቆመው የሦስተኛው የመዘምራን ቡድን መሪ የመራሪ ልጅ ኤታን ነበር፤ የእርሱም የቤተሰብ የትውልድ ሐረግ ከዚህ በታች በተመለከተው አኳኋን እስከ ሌዊ ይደርሳል፦ ኤታን፥ ቂሺ፥ ዐብዲ፥ ማሉክ፥ 45ሐሻብያ፥ አሜስያስ፥ ሒልቂያ፥ 46አሞጺ፥ ባኒ፥ ሼሜር፥ 47ማሕሊ፥ ሙሺ፥ መራሪ፥ ሌዊ።
48ሌዋውያን የሆኑ የእነርሱ ወገኖችም በእግዚአብሔር ቤት ሌላውን ተግባር ሁሉ ያከናውኑ ነበር።
የአሮን ትውልድ
49አሮንና ዘሮቹ የዕጣን መባና በመሠዊያው ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ያቀርቡ ነበር፤ እንዲሁም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የአምልኮ ሥርዓትና እግዚአብሔር የእስራኤልን ኃጢአት ለሚያስተሰርይበት መሥዋዕት ሁሉ ኀላፊዎች ነበሩ፤ እነርሱም ይህን ሁሉ የሚፈጽሙት እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለሙሴ በሰጠው መመሪያ መሠረት ነው። 50የአሮን ዘሮች የትውልድ ሐረግ እንደሚከተለው ነው፦ አልዓዛር፥ ፊንሐስ፥ አቢሹዓ፥ 51ቡቂ፥ ዑዚ፥ ዘራሕያ፥ 52መራዮት፥ አማርያ፥ አሒጦብ፥ 53ሳዶቅ፥ አሒማዓጽ።
ለሌዋውያን የተሰጡ መኖሪያ ስፍራዎች
54ለአሮን ልጆች የተመደቡት የሰፈራ ቦታዎች የሚከተሉት ናቸው፤ የመጀመሪያው ዕጣ ለቃሃት ወገን ስለ ወጣ 55ለእርሱም የተሰጠው ድርሻ በይሁዳ ግዛት የሚገኘው ኬብሮንና በእርሱም ዙሪያ ያለውን የግጦሽ ቦታ ሁሉ ያጠቃልላል። 56የኬብሮን የእርሻ ቦታዎችና መንደሮች ግን ለይፉኔ ልጅ ለካሌብ የተመደቡ ነበሩ። 57-59ለአሮን ልጆች የተመደቡ ከተሞች፥ የመማጠኛ ከተማ የሆነችው ኬብሮን፥ ያቲር፥ ሊብና፥ ኤሽተሞዓ፥ ሒሌን፥ ደቢር፥ ዐሻንና ቤትሼሜሽ ሲሆኑ የግጦሽ ቦታዎቻቸውንም ይጨምራል። 60በብንያም ግዛትም ጌባዕ፥ ዓሌሜትና ዐናቶት ተብለው የሚጠሩት ከተሞች ከነግጦሽ ቦታዎቻቸው ለአሮን ልጆች የተሰጡ ነበሩ፤ እንግዲህ ለአሮን ዘሮች ቤተሰብ ሁሉ መኖሪያ የሚሆኑ በአጠቃላይ ዐሥራ ሦስት ከተሞች ነበሩ። 61በምዕራብ በኩል ከሚገኘው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ግዛት ዐሥር ከተሞች ለቀሩት ለቀዓት ወገን ተሰጡ።
62ለጌርሾን ጐሣም ከይሳኮር፥ ከአሴር፥ ከንፍታሌምና በባሳን ካለው ከምሥራቅ ምናሴ ግዛቶች በአጠቃላይ ዐሥራ ሦስት ከተሞች ለየቤተሰቡ ተመድበው ነበር። 63እንዲሁም ለመራሪ ጐሣ በየወገናቸው ከሮቤል፥ ከጋድና ከዛብሎን ግዛቶች በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ከተሞች በዕጣ ተመድበው ነበር። 64በዚህም ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ ሌዋውያን የሚኖሩባቸውን ከተሞች መደቡላቸው፤ ይህም በየከተማው ዙሪያ ያለውን የግጦሽ ቦታ ያጠቃልላል። 65ከላይ የተጠቀሱት በይሁዳ፥ በስምዖንና በብንያም ግዛቶች ውስጥ የሚገኙት ከተሞች እንደ ሌሎቹ ሁሉ በዕጣ የተመደቡ ነበሩ።
66ከቀዓት ጐሣ አንዳንድ ቤተሰቦች በኤፍሬም ግዛት ውስጥ ከተሞችና የግጦሽ ቦታዎች ተመድበውላቸው ነበር። 67እነርሱም በኤፍሬም ኰረብቶች የምትገኘው የመማጠኛ ከተማ የሆነችው ሴኬም፥ ጌዜር፥ 68ዮቅመዓም፥ ቤትሖሮን፥ 69አያሎንና ጋትሪሞን ከግጦሽ መሬታቸው ጋር ናቸው። 70በምዕራብ በኩል ባለው በምናሴ ግዛት ደግሞ የዓኔርና የቢልዓም ከተሞች በዙሪያቸው ካሉት የግጦሽ ቦታዎች ጋር ለቀሩት ለቀዓት ጐሣ ቤተሰቦች ተመድበውላቸው ነበር።
71ለጌርሾን ጐሣ ቤተሰቦች የሚከተሉት ከተሞች በዙሪያቸው ከሚገኙት የግጦሽ ቦታዎች ጋር ተመድበውላቸው ነበር፦
በምሥራቅ በኩል ካለው ከምናሴ ግዛት በባሳን ያለው ጎላንና ዐስታሮት።
72በይሳኮር ግዛት፥ ቃዴስ፥ ዳበራት፥ 73ራሞትና ዓኔም።
74በአሴር ግዛት ማሻል፥ ዓብዶን፥ 75ሑቆቅና ረሖብ፤
76በንፍታሌም ግዛት በገሊላ ምድር የምትገኘው ቄዴሽ፥ ሐሞንና ቂርያታይም፤
77ለቀሪዎቹ የመራሪ ጐሣ ቤተሰቦች የሚከተሉት ከተሞች በዙሪያቸው ከሚገኙት የግጦሽ ቦታዎች ጋር ተመድበውላቸው ነበር፦
በዛብሎን ግዛት ሪሞኖና ታቦር፤
78ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ፥ ከኢያሪኮ ማዶ ባለው በሮቤል ግዛት በከፍተኛ ሜዳ ላይ የምትገኘው ቤጼር፥ ያህጻ፥ 79ቀዴሞትና ሜፋዓት፤
80በጋድ ግዛት በገለዓድ የምትገኘው ራሞት፥ ማሕናይም፥ 81ሐሴቦንና ያዕዜር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ