አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 27

27
ወታደራዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች
1ከዚህ በታች የተመለከተው የእስራኤላውያን የቤተሰብ አለቆችና የጐሣ መሪዎች፥ እንዲሁም ዓመቱን በሙሉ በየወሩ ንጉሡንና ሕዝቡን የሚያገለግሉ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆችና አዛዦቻቸው ስም ዝርዝር ነው። እያንዳንዱ ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩት።
2-15ለእያንዳንዱም ወር የቡድን መሪ የነበሩት ስማቸው ከዚህ በታች የተዘረዘረው ነው፦
በመጀመሪያው ወር በአንደኛው ክፍል የበላይ የሆነው የዛብዲኤል ልጅ ያሾብዓም ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ፤ እርሱም የይሁዳ ነገድ ክፍል የሆነው የፋሬስ ጐሣ አባል ነበር።
በሁለተኛው ወር ክፍል ላይ የበላይ የነበረው አሖሓዊው ዶዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ፤ ሚቅሎትም የእርሱ ምክትል ነበር።
በሦስተኛው ወር ሦስተኛው የሠራዊት አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያ ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ ይህ በናያ በሠላሳው መካከል ኀያል ሆኖ የሠላሳው አለቃ ነበረ። ልጁ ዓሚዛባድ የክፍሉ አዛዥ ነበር።
በአራተኛው ወር በአራተኛው ክፍል የበላይ የሆነው የኢዮአብ ወንድም ዐሣሄል ነበር። ልጁም ዜባድያ የእርሱ ተተኪ ሆነ። በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በአምስተኛው ወር፥ በአምስተኛው ክፍል የበላይ ይጅሃራዊው ሻምሁት ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በስድስተኛው ወር፥ በስድስተኛው ክፍል የበላይ ተቆዓዊው የዒቄሽ ልጅ ዒራ ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በሰባተኛው ወር፥ በሰባተኛው ክፍል የበላይ ከኤፍሬም ነገድ ፐሎናዊ የሆነው ሔሌጽ ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በስምንተኛው ወር፥ በስምንተኛው ክፍል የበላይ የሑሻ ተወላጅ የነበረው ሲበካይ ነበር፤ እርሱም የይሁዳ ነገድ ከነበረው ከዛራ ዘር ነበር። በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በዘጠነኛው ወር፥ በዘጠነኛው ክፍል የበላይ ከብንያም ነገድ የነበረው ዓናቶታዊው አቢዔዜር ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በዐሥረኛው ወር፥ በዐሥረኛው ክፍል የበላይ ከዛራ ነገድ የነጦፋ ተወላጅ የሆነው ማሕራይ ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በዐሥራ አንደኛው ወር፥ በዐሥራ አንደኛው ክፍል የበላይ ከኤፍሬም ተወላጅ ነገድ የጆርቶን ተወላጅ በናያ ነበር፤ በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
በዐሥራ ሁለተኛው ወር በዐሥራ ሁለተኛው ክፍል የበላይ የዖትኒኤል ጐሣ የነጦፋ ተወላጅ የነበረው ሔልዳይ ነበር። በእርሱም ክፍል ኻያ አራት ሺህ ተረኞች ነበሩ።
የእስራኤል ነገዶች አስተዳደር
16-22የእስራኤል ነገዶች አስተዳዳሪዎች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦
የሮቤል ነገድ አስተዳዳሪ፦ የዚክሪ ልጅ ኤሊዔዘር
የስምዖን ነገድ አስተዳዳሪ፦ የማዕካ ልጅ ሸፋጥያ
የሌዊ ነገድ አስተዳዳሪ፦ የቀሙኤል ልጅ ሐሻብያ
የአሮን ነገድ አስተዳዳሪ፦ ሳዶቅ
የይሁዳ ነገድ አስተዳዳሪ፦ ከንጉሥ ዳዊት ወንድሞች አንዱ የሆነው ኤሊሁ
የይሳኮር ነገድ አስተዳዳሪ፦ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ
የዛብሎን ነገድ አስተዳዳሪ፦ የአብድዩ ልጅ ዩሽማዕያ
የንፍታሌም ነገድ አስተዳዳሪ፦ የዐዝርኤል ልጅ ያሪሞት
የኤፍሬም ነገድ አስተዳዳሪ፦ የዐዛዝያ ልጅ ሆሴዕ
የምዕራባዊ የምናሴ ነገድ እኩሌታ አስተዳዳሪ፦ የፐዳያ ልጅ ኢዮኤል
የምሥራቃዊ የምናሴ ነገድ እኩሌታ አስተዳዳሪ፦ የዘካርያስ ልጅ ዩዶ
የብንያም ነገድ አስተዳዳሪ፦ የአበኔር ልጅ ያዕሲኤል
የዳን ነገድ አስተዳዳሪ፦ የይሮሐም ልጅ ዐዛርኤል።
23እግዚአብሔር “የእስራኤልን ሕዝብ እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ” ሲል በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ንጉሥ ዳዊት ዕድሜአቸው ከኻያ ዓመት በታች የሆኑትን በሕዝብ ቈጠራ ውስጥ አላስገባቸውም ነበር፤ #ዘፍ. 15፥5፤ 22፥17፤ 26፥4። 24የጸሩያ ልጅ ኢዮአብ የሕዝብ ቈጠራ ማድረግ ጀምሮ ሳይጨርስ ቀርቶ ነበር፤ በዚህ በሕዝብ ቈጠራ ምክንያት እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ቀጥቶ ስለ ነበር የመጨረሻው ቊጥር በንጉሥ ዳዊት መንግሥት የታሪክ መዝገብ ውስጥ አልተመዘገበም ነበር። #2ሳሙ. 24፥1-15፤ 1ዜ.መ. 21፥1-14።
የቤተ መንግሥት ንብረት አስተዳዳሪዎች
25-31የቤተ መንግሥት ንብረት ኀላፊዎች የሆኑት ሰዎች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦
የቤተ መንግሥት ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ የዐዲኤል ልጅ ዓዝማዌት
በየገጠሩ፥ በየከተማው፥ በየመንደሩ በየምሽጉ የሚገኙ የመንግሥት ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ፦ የዑዚያ ልጅ ዮናታን
የግብርና ሥራ ኀላፊ፦ የከሉብ ልጅ ዔዝሪ
የወይን ተክል ቦታዎች ኀላፊ የራማ ተወላጅ የሆነው ሺምዒ
የወይን ጠጅ ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ፦ የሸፋም ተወላጅ የሆነው ዛብዲ
በደቡባዊ ኰረብቶች የሚገኙት የወይራና የወርካ ዛፎች ኀላፊ፦ የጌዴር ተወላጅ የሆነው ባዓልሐናን
የወይራ ዘይት ግምጃ ቤት ኀላፊ ኢዮአስ
በሳሮን ሜዳ የሚገኙት የቀንድ ከብቶች ኀላፊ የሳሮን ተወላጅ የሆነው ሺጥራይ
በሸለቆዎች የሚገኙ የቀንድ ከብቶች አስተዳዳሪ፦ የዓድላይ ልጅ ሻፋጥ
የግመሎች ኀላፊ፦ እስማኤላዊው ኦቢል
የአህዮች ኀላፊ፦ የሜሮኖት ተወላጅ የሆነው ዬሕድያ
የበጎችና የፍየሎች ኀላፊ፦ ሀግራዊው ያዚዝ።
የዳዊት የግል አማካሪዎች
32የንጉሥ ዳዊት አጐት የሆነው ዮናታን ብልኅ አማካሪና የታወቀ ምሁር ነበር፤ እርሱና የሐክሞኒ ልጅ ይሒኤል የንጉሡ ልጆች አስተማሪዎች ነበሩ፤ 33አኪጦፌል የንጉሡ አማካሪ ሲሆን፥ አርካዊው ሑሻይ የንጉሡ ወዳጅ ነበር፤ 34አኪጦፌል ከሞተ በኋላም አብያታርና የበናያ ልጅ ይሆያዳዕ የንጉሡ አማካሪዎች ሆኑ፤ ኢዮአብ ደግሞ የንጉሡ ሠራዊት አዛዥ ነበር።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ