አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26
26
የቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎች
1የቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎች የሆኑ ሌዋውያን የሥራ ምድብ እንደሚከተለው ነው፦ ከቆሬ ጐሣ ከአሳፍ ቤተሰብ የቆሬ ልጅ መሼሌምያ ነበር። 2እርሱም ሰባት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በዕድሜአቸው ተራ ዘካርያስ፥ ይዲዕኤል፥ ዘባድያ፥ ያትኒኤል፥ 3ዔላም፥ የሆሐናንና ኤልየሆዔናይ ተብለው የሚጠሩት ናቸው።
4ስምንት ወንዶች ልጆችን በመስጠት እግዚአብሔር የባረከው ዖቤድኤዶም የተባለም ሌላ ሰው ነበር፤ ልጆቹም በዕድሜአቸው ተራ ሸማዕያ፥ ይሆዛባድ፥ ዮአሕ፥ ሳካር፥ ናትናኤል፥ 5ዓሚኤል፥ ይሳኮርና ፐዑልታይ ተብለው የሚጠሩት ናቸው። #2ሳሙ. 6፥11፤ 1ዜ.መ. 13፥14።
6-7የዖቤድኤዶም የበኲር ልጅ ሸማዕያ ስድስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ዖትኒ፥ ረፋኤል፥ ዖቤድ፥ ኤልዛባድ ኤሊሁና ሰማክያ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ እነርሱም ስለ ነበራቸው ታላቅ ችሎታ በጐሣቸው መሪዎች ነበሩ፤ በተለይ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ከፍ ያለ ችሎታ ነበራቸው።
8እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩ፦ እነርሱና ልጆቻቸው እንዲሁም ዘመዶቻቸው የሥራ ችሎታና ሥራውን የመሥራት ጥንካሬ ነበራቸው፤ የዖቤድኤዶም ልጆችና የልጅ ልጆች በጠቅላላው ሥልሳ ሁለት ነበሩ።
9መሼሌምያም ችሎታ ያላቸው ዐሥራ ስምንት ልጆችና ቤተሰቦች ነበሩት።
10ከመራሪ ጐሣ አራት ወንዶች ልጆች የነበሩት ሖሳ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር፤ ልጆቹም፥ ምንም እንኳ የበኲር ልጅ ባይሆንም አባቱ መሪ ያደረገው ሺምሪ፥ 11ሒልቂያ፥ ጠባልያና ዘካርያስ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፤ ከሖሳ ቤተሰብ የቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎች የሆኑ በድምሩ ዐሥራ ሦስት አባላት ነበሩ።
12የቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎች በየቤተሰቡ በቡድን ተከፍለው ነበር፤ እነርሱም ልክ እንደ ሌሎቹ ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ አገልግሎት ነበራቸው፤ 13ሽማግሌ ወይም ወጣት ሳይባል በእኩልነት እንደየቤተሰባቸው ለያንዳንዱ በር ጥበቃ ዕጣ ይጣል ነበር። 14ሼሌምያ በምሥራቅ በኩል የሚገኘውን ቅጽር በር ለመጠበቅ ዕጣ ወጣለት፤ ዘወትር መልካም ምክር ይሰጥ የነበረው ልጁ ዘካርያስ ደግሞ በሰሜን በኩል የሚገኘውን ቅጽር በር ለመጠበቅ ዕጣ ወጣለት፤ 15ለዖቤድኤዶም በደቡብ በኩል የሚገኘው ቅጽር በር ደረሰው፤ ልጆቹም የዕቃ ግምጃ ቤቶችን ለመጠበቅ ተመደቡ፤ 16ለሹፒምና ለሖሳ በምዕራብ በኩል የሚገኘው ቅጽር በርና በላይኛው መንገድ በኩል የሚገኘው ሻሌኬት ተብሎ የሚጠራው ቅጽር በር ደረሳቸው፤ የዘብ ጥበቃው አገልግሎት በክፍለ ጊዜ የተመደበ ሆኖ ቅደም ተከተል ተራ የያዘ ነበር፤ 17በየቀኑ በምሥራቅ በኩል ስድስት፥ በሰሜን አራት፥ በደቡብ አራት ዘብ ጠባቂዎች ይመደባሉ፤ እንዲሁም በየቀኑ አራት ዘብ ጠባቂዎች የዕቃ ግምጃ ቤቶቹን ለመጠበቅ ሲመደቡ፥ ከእነርሱ ሁለቱ አንዱን የዕቃ ግምጃ ቤት፥ ሁለቱ ደግሞ ሌላውን ይጠብቁ ነበር። 18በምዕራብ በኩል መንገዱን ተጠግቶ በተሠራው አደባባይ አጠገብ አራት ዘብ ጠባቂዎች ሲመደቡ፥ ራሱን አደባባዩን የሚጠብቁ ሁለት ዘብ ጠባቂዎች ተመድበው ነበር። 19እንግዲህ ለቆሬና ለመራሪ ጐሣዎች የተመደበላቸው የዘብ ጥበቃ አገልግሎት ይህ ነበር።
ቀሪው የቤተ መቅደስ አገልግሎት
20ከሌዋውያን መካከል አኪያ የቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤትና ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የሚቀርቡት ዕቃዎች ለሚከማቹባቸው ቤቶች ኀላፊ ነበር፤ 21ላደን ከጌርሾን ጐሣ የነበረ ሲሆን እርሱም የይሒኤል አባት ነበር፤ ከእርሱ ተወላጆች ብዙዎቹ በየወገናቸው የቤተሰብ አለቆች ነበሩ። 22ዜታምና ኢዮኤል የተባሉት የይሒኤል ሌሎች ሁለት ልጆች የቤተ መቅደሱ ቤተ መዛግብትና የዕቃ ግምጃ ቤቶች ኀላፊዎች ነበሩ። 23ለዓምራም፥ ለይጽሃር፥ ለኬብሮንና ለዑዚኤል ዘሮች የሥራ ድርሻ ተሰጥቶአቸው ነበር።
24የሙሴ ልጅ የጌርሾም ጐሣ የሆነው ሸቡኤል ለቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ኀላፊዎች ለሆኑት የበላይ ባለሥልጣን ነበር፤ 25እርሱም በጌርሾም ወንድም በኤሊዔዘር በኩል ለሸሎሚት የሥጋ ዝምድና ነበረው፤ ኤሊዔዘር ረሐብያን ወለደ፤ ረሐብያም ይሻዕያን ወለደ፤ ይሻዕያ ዮራምን ወለደ፤ ዮራምም ዚክሪን ወለደ፤ ዚክሪም ሼሎሚትን ወለደ፤ 26ሸሎሚትና ዘመዶቹ ንጉሥ ዳዊት የቤተሰብ አለቆች፥ የጐሣ ቡድን መሪዎችና የጦር መኰንኖች ለእግዚአብሔር የተለዩ አድርገው ላቀረቡአቸው ስጦታዎች ኀላፊዎች ነበሩ፤ 27እነዚህ ኀላፊዎችም በጦርነት ጊዜ ከተገኘው ምርኮ ጥቂቱን ወስደው ለቤተ መቅደሱ ሥራ የተለየ እንዲሆን ያደርጉ ነበር። 28ሸሎሚትና ዘመዶቹ ለቤተ መቅደስ ሥራ ለተለዩ ነገሮች ሁሉ፥ በነቢዩ ሳሙኤል፥ በንጉሥ ሳኦል፥ በኔር ልጅ አበኔርና በጸሩያ ልጅ ኢዮአብ ላቀረቡአቸው ስጦታዎች ጭምር ኀላፊዎች ነበሩ።
የሌሎች ሌዋውያን የሥራ ድርሻ
29ከይጽሃር ልጆች መካከል፥ ከናንያና ልጆቹ ከቤተ መቅደሱ ውጪ በመንግሥት ሥራ ሹማምንትና ዳኞች ሆነው ተሹመው ነበር።
30ከኬብሮናውያን ወገን ሐሻብያና ወንድሞቹ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ከዮርዳኖስ በስተምዕራብ ባለው በእስራኤል አገር ለመንፈሳዊ ሥራና ለመንግሥት አገልግሎት ኀላፊዎች ሆነው ተመደቡ። 31ከኬብሮናውያንም በቤተሰብ የትውልድ ምዝገባ መሠረት ይሪያ አለቃቸው ነበር፤ ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት በመዝገቡ ውስጥ ፍለጋ ተደርጎ በገለዓድ ያዕዜር ችሎታ ያላቸው ኬብሮናውያን ተገኙ፤ 32ንጉሥ ዳዊት ከእነዚያ ዘመዶች መካከል ምርጥ የሆኑ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ የቤተሰብ አለቆችን መረጠ፤ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ማለትም በሮቤል፥ በጋድና በምናሴ ነገድ እኩሌታ ግዛቶች መንፈሳዊውንና ዓለማዊውን ጉዳይ ሁሉ የማስተዳደር ኀላፊነት ሰጣቸው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 26: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997