የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11

11
ዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ሆነ
(2ሳሙ. 5፥1-10)
1እስራኤላውያን ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት ሄደው እንዲህ አሉት፦ “እኛ ሁላችን የሥጋ ዘመዶችህ ነን፤ 2ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እንኳ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ጦርነት የምትመራ አንተ ነበርክ፤ ‘ሕዝቤን እስራኤልን የምትመራና የምታስተዳድር አንተ ነህ’ ብሎ አምላክህ እግዚአብሔር ነግሮሃል።” 3በዚያም ዐይነት የእስራኤል መሪዎች ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ንጉሥ ዳዊት መጡ፤ እርሱም ከእነርሱ ጋር የተቀደሰ ስምምነት አደረገ፤ እግዚአብሔር በሳሙኤል አማካይነት በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ሕዝቡ ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።
ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል ማድረጉ
4ንጉሥ ዳዊትና መላው የእስራኤል ሕዝብ ሄደው በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ አደጋ ጣሉ፤ በዚያን ጊዜ የከተማይቱ ስም “ኢያቡስ” ይባል ነበር፤ በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት ኢያቡሳውያን ናቸው። #ኢያሱ 15፥63፤ መሳ. 1፥21። 5ኢያቡሳውያን ዳዊትን “ከቶ ወደዚህ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን በጽዮን የሠሩትን ምሽጋቸውን ያዘ፤ ከዚያም በኋላ ያቺ ስፍራ “የዳዊት ከተማ” ተብላ ትጠራ ጀመር። 6ዳዊትም “በመጀመሪያ በኢያቡሳውያን ላይ አደጋ የሚጥል ሰው የሠራዊቱ አዛዥ ይሆናል!” አለ፤ የጸሩያ ልጅ ኢዮአብ በመጀመሪያ ሄዶ በኢያቡሳውያን ላይ አደጋ በመጣሉ የሠራዊቱ አዛዥ ሆነ፤ 7ዳዊትም ሄዶ በምሽጉ ውስጥ ስለ ኖረ ያቺ ስፍራ “የዳዊት ከተማ” ተብላ ተጠራች። 8ዳዊት ከኰረብታው በስተ ምሥራቅ በኩል በዐፈር ከተደለደለው ስፍራ አንሥቶ ከተማይቱን እንደገና ሠራ፤ ኢዮአብም በበኩሉ የቀረውን የከተማይቱን ክፍል ሠራ፤ 9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በመሆኑ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።
ዝነኞች የሆኑት የዳዊት ወታደሮች
(2ሳሙ. 23፥8-39)
10ዝነኞች የሆኑት የዳዊት ወታደሮች ስም ዝርዝር ከዚህ በታች እንደሚከተለው ነው፦ እነርሱም ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነው እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ዳዊት እንዲነግሥ በጣም ረድተዋል። መንግሥቱም ጽኑና ኀያል እንዲሆን አድርገዋል።
11የመጀመሪያው የሐክሞን ጐሣ ወገን የሆነው ያሾብዓም ሲሆን፥ እርሱም የሦስቱ ኀያላን መሪ ነበር፤ እርሱ በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን አንሥቶ በአንድ ፍልሚያ ብቻ ሁሉንም ገደላቸው፤ 12ከእርሱ የሚቀጥል ከሦስቱ ኀያላን አንዱ የሆነው ሌላው ከአሖሕ ጐሣ የዶዶ ልጅ አልዓዛር ነው፤ 13እርሱ ፍልስጥኤማውያን ለጦርነት በተሰለፉ ጊዜ በፓስደሚም ከዳዊት ጋር ነበር፤ የገብስ ማሳ በነበረበት ቦታ እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 14እርሱና ተከታዮቹ በዚያው በማሳው ውስጥ ፍልስጥኤማውያንን ተቋቊመው ወጉአቸው፤ እግዚአብሔርም ታላቅ ድልን አጐናጸፋቸው።
15አንድ ቀን ከሠላሳዎቹ ጀግኖች ሦስቱ ወታደሮች ፍልስጥኤማውያን በራፋይም ሸለቆ ሰፍረው በነበረበት ጊዜ፥ ዳዊት በሚኖርበት በአዱላም ዋሻ አጠገብ ወዳለው አለት ሄዱ፤ 16ዳዊት በዚያን ጊዜ፥ በተመሸገ ኰረብታ ላይ ነበር፤ ከፍልስጥኤማውያን ሠራዊት አንዱ ቡድን ቤተልሔምን በመውረር ያዘ። 17ዳዊትም “በቤተልሔም ቅጽር በር አጠገብ ካለው የውሃ ጒድጓድ የምጠጣው ውሃ ማን በሰጠኝ!” ብሎ ተመኘ። 18በዚህን ጊዜ ሦስቱ ዝነኛ ወታደሮች የፍልስጥኤማውያንን ሰፈር ጥሰው በማለፍ ከጒድጓዱ ውሃ ቀዱና ለዳዊት ይዘውለት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጠጣው አልወደደም፤ በዚህ ፈንታ ለእግዚአብሔር እንደ መባ አድርጎ አፈሰሰው። 19“እኔ ይህን ውሃ መጠጣት ከቶ አልችልም! እኔ ይህን ውሃ ብጠጣ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚያን ኀያላን ሰዎች ደም እንደ ጠጣሁ ይቈጠራል!” አለ። ስለዚህም ውሃውን ይጠጣ ዘንድ አልወደደም፤ እንግዲህ ዝነኞች የሆኑት ሦስቱ ኀያላን ወታደሮች የፈጸሙአቸው የጀግንነት ተግባሮች እነዚህ ናቸው።
20የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ዝነኞች ወታደሮች የበላይ አለቃ ነበር፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰዎችን ገድሎ ስለ ነበር እንደ ሦስቱ ዝነኞች ወታደሮች ታዋቂ ሆነ፤ 21ከሦስቱ ጀግኖች መካከል እንደ አንዱ ባይቈጠርም በሠራው ጀብዱ ከእነርሱ ይበልጥ እጥፍ ድርብ ክብር በማግኘቱ የእነርሱ አለቃ ለመሆን በቃ። #11፥21 ከሦስቱ ወይም ከሠላሳው።
22በቃብጽኤል ምድር የዮዳሄ ልጅ በናያ ዝነኛ ወታደር ነበር፤ እርሱ ሁለት የታወቁ ሞአባውያን ጦረኞችን ከመግደሉም ሌላ ብዙ የጀግንነት ሥራ ፈጽሞአል፤ አንድ ጊዜ በምድር ላይ ዐመዳይ በወረደበት ቀን ወደ አንድ ዋሻ ወርዶ አንበሳ ገደለ፤ 23እንዲሁም በጣም ትልቅ ጦር ይዞ የነበረውን፥ ቁመቱ ከሁለት ሜትር በላይ የሆነውን፥ አንድ ግዙፍ ግብጻዊ ገድሎአል፤ ይኸውም በናያ በእጁ ከበትር በስተቀር ሌላ የጦር መሣሪያ ሳይዝ ወደ ግብጻዊው ቀርቦ ከመታው በኋላ ግብጻዊው ይዞት የነበረውን የሸማኔ መጠቅለያ የሚመስለውን የገዛ ጦሩን ቀምቶ ገደለው። 24እንግዲህ ከሠላሳዎቹ አንዱ የሆነው በናያ የፈጸማቸው የጀግንነት ሥራዎች እነዚህ ናቸው፤ #11፥24 ከሠላሳዎቹ ወይም ከሦስቱ 25ከሠላሳዎቹ መካከል እጅግ ታዋቂ ቢሆንም በዝነኛነቱ ከሦስቱ ኀያላን ጀግኖች ደረጃ አልደረሰም፤ ዳዊትም በናያን የክብር ዘብ አዛዥ በማድረግ ሾሞት ነበር።
26-47ከሠላሳዎቹ መካከል የሌሎቹ ሰዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦
የኢዮአብ ወንድም ዐሣሄል፥
የቤተልሔሙ ተወላጅ የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፥
የሐሮድ ተወላጅ ሻሞት፥
የፌሌጥ ተወላጅ የሆነው ሔሌጽ፥
የተቆዓ ተወላጅ የሆነው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፥
የዐናቶት ተወላጅ የሆነው አቢዔዜር፥
የሑሻ ተወላጅ የሆነው ሲበካይ፥
የአሖሕ ተወላጅ የሆነው ዒላይ፥
የነጦፋ ተወላጅ የሆነው ማህራይ፥
የነጦፋ ተወላጅ የሆነው የባዕና ልጅ ሔሌድ፥
በብንያም ግዛት የምትገኘው የጊብዓ ተወላጅ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥
የፒርዓቶን ተወላጅ የሆነው በናያ፥
በጋዓሽ አጠገብ ባሉት ሸለቆዎች የተወለደው ሑራይ፥
የዓረባ ተወላጅ የሆነው አቢኤል፥
የባሕሩም ተወላጅ የሆነው ዓዝማዌት፥
የሻዓልቦን ተወላጅ የሆነው ኤልያሕባ፥
የጊዞን ተወላጅ የሆነው ሃሼም፥
የሃራር ተወላጅ የሆነው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥
የሀራር ተወላጁ የሳካር ልጅ አሒአም፥
የኡር ልጅ ኤሊፋል፥
የመኬራ ተወላጅ የሆነው ሔፌር፥
የፐሎን ተወላጅ የሆነው አሒያ፥
የቀርሜሎስ ተወላጅ የሆነው ሔጽሮ፥
የኤዝባይ ልጅ ናዕራይ፥
የናታን ወንድም ዮኤል፥
የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፥
የዐሞን ተወላጅ የሆነው ጼሌቅ፥
የበኤሮት ተወላጅና የኢዮአብ ጋሻጃግሬ የነበረው ናሕራይ፥
የያቲር ተወላጆች የሆኑት ዒራና ጋሬብ፥
ሒታዊው ኦርዮን፥
የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥
የሺዛ ልጅ ዐዲና፤ (ይህ ሰው የራሱ ቡድን የሆኑ ሠላሳ ወታደሮችን እንደ ያዘ ከሮቤል ነገድ የታወቀ ነበር፤)
የማዕካ ልጅ ሐናን፥
የሚታን ተወላጅ የሆነው ኢዮሣፍጥ፥
የዐሽተራ ተወላጅ የሆነው ዑዚያ፥
የዓሮዔር ተወላጅ የሆነው የሆታም ልጆች ሻማዕና ይዒኤል፥
የቲጺ ተወላጅ የሆነው የሺምሪ ልጆች ይዲዕኤልና ዮሐ፥
የማሐዋ ተወላጅ የሆነው ኤሊኤል፥
የኤልናዓም ልጆች ይሪባይና ዮሻውያ፥
የሞአብ ተወላጅ የሆነው ዩትማ፥
የጾባ ተወላጆች የሆኑት ኤሊኤል፥ ዖቤድና ያዕሲኤል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ