ገና ደካሞች ሳለን፣ ልክ ጊዜው ሲደርስ፣ ክርስቶስ ስለ ኀጢአተኞች ሞቷልና። ለጻድቅ የሚሞት ሰው ማግኘት እጅጉን ያዳግታል፤ ለደግ ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል። አሁን በደሙ ከጸደቅን፣ ይልቁንማ በርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቍጣ እንዴት አንድንም! የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከርሱ ጋራ ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን። ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቷል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ! ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ አንዱ ሰው የኀጢአት ውጤት አይደለም፤ ምክንያቱም ፍርዱ የአንድን ሰው ኀጢአት ተከትሎ ኵነኔን አመጣ፤ ስጦታው ግን አያሌ መተላለፍን ተከትሎ ጽድቅን አመጣ። በአንድ ሰው መተላለፍ ምክንያት ሞት በዚህ ሰው በኩል የነገሠ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን የተትረፈረፈ ጸጋና የጽድቅ ስጦታ የተቀበሉት፣ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንዴት አብልጠው በሕይወት አይነግሡ! ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። ሕግ በመምጣቱ መተላለፍ በዛ፤ ነገር ግን ኀጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ፤ ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።
ሮሜ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ሮሜ 5
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሮሜ 5:6-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos