ሮሜ 10:8-17

ሮሜ 10:8-17 NASV

ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና። መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ? ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኗል?” ብሏልና። እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው።