የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 18:17-24

ራእይ 18:17-24 NASV

ያ ሁሉ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፋ።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞች ሁሉ፣ የመርከብ ሠራተኞችና ኑሯቸውን በባሕር ላይ የመሠረቱ ሁሉ በሩቅ ይቆማሉ። እርሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጢስ ሲያዩ፣ ‘እንደዚህች ያለ ታላቅ ከተማ ከቶ የት አለ?’ እያሉ ይጮኻሉ። በራሳቸውም ላይ አቧራ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ብለው ጮኹ፤ “ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያላቸው ሁሉ፣ በርሷም ሀብት የበለጸጉ፣ ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ውስጥ ጠፍታለች!’ “ሰማይ ሆይ፤ በርሷ ላይ ሐሤት አድርግ! ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ሐሤት አድርጉ! በእናንተ ላይ ባደረሰችው ነገር እግዚአብሔር ፈርዶባታልና።” ከዚያም አንድ ብርቱ መልአክ፣ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው፤ እንዲህም አለ፤ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን፣ እንዲህ ባለ ኀይል ትወረወራለች፤ ተመልሳም አትገኝም። የበገና ደርዳሪዎችና የሙዚቀኞች ድምፅ፣ የዋሽንትና የመለከት ነፊዎች ድምፅ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምፅም፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም። የመብራት ብርሃን፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፤ በአስማትሽም ሕዝቦች ሁሉ ስተዋል። በርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን፣ በምድርም የተገደሉት ሁሉ ደም ተገኘ።”