ራእይ 16
16
ሰባቱ የእግዚአብሔር ቍጣ ጽዋዎች
1ከዚያም ለሰባቱ መላእክት፣ “ሂዱ፤ ሰባቱን የእግዚአብሔር ቍጣ ጽዋዎች በምድር ላይ አፍስሱ” የሚል ታላቅ ድምፅ ከቤተ መቅደሱ ሰማሁ።
2የመጀመሪያው መልአክ ሄዶ ጽዋውን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውን ምልክት በተቀበሉትና ለምስሉም በሰገዱት ሰዎች ላይ ክፉኛ የሚያሠቃይ ቍስል ወጣባቸው።
3ሁለተኛው መልአክ ጽዋውን በባሕር ላይ አፈሰሰ፤ ባሕሩም እንደ ሞተ ሰው ደም ሆነ፤ በባሕሩ ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሞቱ።
4ሦስተኛው መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ላይ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። 5ከዚያም በውሆች ላይ ሥልጣን ያለው መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
“ያለህና የነበርህ ቅዱሱ ሆይ፤
እንዲህ ስለ ፈረድህ፣
አንተ ጻድቅ ነህ፤
6የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ፣
አንተም ደግሞ ደም እንዲጠጡ አደረግሃቸው፤ ይህ የሚገባቸው ነውና።”
7እንዲሁም ከመሠዊያው እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፤
“አዎን፤ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤
ፍርድህ እውነትና ጽድቅ ነው።”
8አራተኛውም መልአክ ጽዋውን በፀሓይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሓይም ሰዎችን በእሳት እንድታቃጥል ኀይል ተሰጣት። 9እነርሱም በታላቅ ሐሩር ተቃጠሉ፤ በእነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ እንጂ ንስሓ አልገቡም፤ ክብርም አልሰጡትም።
10አምስተኛውም መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት በጨለማ ተዋጠ፤ ሰዎችም ከሥቃያቸው የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር፤ 11ደግሞም ከሥቃያቸውና ከቍስላቸው የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ እንጂ ከሥራቸው ንስሓ አልገቡም።
12ስድስተኛውም መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸው የወንዙ ውሃ ደረቀ። 13ከዚያም ከዘንዶው አፍ፣ ከአውሬው አፍና ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ እንቍራሪት የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ። 14እነርሱም ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት እንዲሰበስቧቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይሄዳሉ።
15 “እነሆ፤ እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ ዕራቍቱን እንዳይሆን ኀፍረቱም እንዳይታይ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው ብፁዕ ነው።”
16እነርሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።
17ሰባተኛውም መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ አፈሰሰ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካለው ዙፋንም “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ወጣ። 18ከዚያም መብረቅ፣ ድምፅ፣ ነጐድጓድና ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ላይ ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ የምድር መናወጥ ታይቶ አይታወቅም፤ ነውጡም እጅግ ታላቅ ነበር። 19ታላቂቱ ከተማ ከሦስት ተከፈለች፤ የሕዝቦች ከተሞችም ፈራረሱ፤ እግዚአብሔርም ታላቂቱን ባቢሎን አስታወሰ፤ በብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የተሞላውን ጽዋ ሰጣት። 20ደሴቶች ሁሉ ሸሹ፤ ተራሮችም ሊገኙ አልቻሉም። 21በሚዛን ሲመዘን እያንዳንዱ አርባ አምስት ኪሎ ግራም#16፥21 ግሪኩ አንድ ታላንት ይለዋል። የሚሆን ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ መቅሠፍቱ እጅግ አሠቃቂ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ከበረዶው መቅሠፍት የተነሣ እግዚአብሔርን ተሳደቡ።
Currently Selected:
ራእይ 16: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.