የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 73:15-28

መዝሙር 73:15-28 NASV

“እኔ እንደዚህ እናገራለሁ” ብልማ ኖሮ፣ የልጆችህን ትውልድ በከዳሁ ነበር። ይህን ነገር ለመረዳት በሞከርሁ ጊዜ፣ አድካሚ ተግባር መስሎ ታየኝ። ይኸውም ወደ አምላክ መቅደስ እስክገባ፣ መጨረሻቸውንም እስካይ ድረስ ነበር። በርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አስቀመጥሃቸው፤ ወደ ጥፋትም አወረድሃቸው። እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ! በድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ። ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣ ጌታ ሆይ፤ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣ እንደ ቅዠት ከንቱ ታደርጋቸዋለህ። ነፍሴ በተማረረች ጊዜ፣ ልቤም በተቀሠፈ ጊዜ፣ ደነዝና አላዋቂ ሆንሁ፤ በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ። ይህም ሆኖ ዘወትር ከአንተ ጋራ ነኝ፤ አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል። በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ። በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም። ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣ የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው። እነሆ፤ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፤ አንተ የሚያመነዝሩትን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ። ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ ጌታ እግዚአብሔርን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ፤ ስለ ሥራህም ሁሉ እናገር ዘንድ።