መዝሙር 73:15-28
መዝሙር 73:15-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እኔ እንደዚህ እናገራለሁ” ብልማ ኖሮ፣ የልጆችህን ትውልድ በከዳሁ ነበር። ይህን ነገር ለመረዳት በሞከርሁ ጊዜ፣ አድካሚ ተግባር መስሎ ታየኝ። ይኸውም ወደ አምላክ መቅደስ እስክገባ፣ መጨረሻቸውንም እስካይ ድረስ ነበር። በርግጥ በሚያዳልጥ ስፍራ አስቀመጥሃቸው፤ ወደ ጥፋትም አወረድሃቸው። እንዴት ፈጥነው በቅጽበት ጠፉ! በድንጋጤ ፈጽመው ወደሙ። ሰው ከሕልሙ ሲነቃ እንደሚሆነው፣ ጌታ ሆይ፤ አንተም በምትነሣበት ጊዜ፣ እንደ ቅዠት ከንቱ ታደርጋቸዋለህ። ነፍሴ በተማረረች ጊዜ፣ ልቤም በተቀሠፈ ጊዜ፣ ደነዝና አላዋቂ ሆንሁ፤ በፊትህም እንደ እንስሳ ሆንሁ። ይህም ሆኖ ዘወትር ከአንተ ጋራ ነኝ፤ አንተም ቀኝ እጄን ይዘኸኛል። በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ። በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም። ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣ የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው። እነሆ፤ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፤ አንተ የሚያመነዝሩትን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ። ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ ጌታ እግዚአብሔርን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ፤ ስለ ሥራህም ሁሉ እናገር ዘንድ።
መዝሙር 73:15-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነርሱ እንደሚናገሩት ለመናገር ባስብ ኖሮ ለሕዝብህ ታማኝ ባልሆንኩም ነበር፤ ይህን ለመረዳት ኅሊናዬን አነቃሁ፤ ነገር ግን በጣም አስቸጋሪ ሆኖ አገኘሁት። ወደ መቅደስህ እስክገባ ድረስ ምንም ማወቅ አልቻልኩም፤ ወደ መቅደስህ በገባሁ ጊዜ ግን በክፉዎች ላይ ምን እንደሚደርስባቸው ተረዳሁ። በሚያዳልጥ ስፍራ ታኖራቸዋለህ፤ ወድቀው እንዲጠፉም ታደርጋቸዋለህ። በቅጽበት ተደመሰሱ፤ መጨረሻቸውም አስደንጋጭ ሆነ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ስትነሣ እነርሱ በማለዳ እንደሚረሳ ሕልም ይጠፋሉ። ኅሊናዬን በጣም መረረው፤ ልቤም ተሰበረ። ጌታ ሆይ! እኔ ለአንተ ከእንስሶች የማልሻል፥ ምንም የማይገባኝ አላዋቂ ነበርኩ። ነገር ግን ዘወትር ከአንተ ጋር እኖራለሁ፤ አንተም ቀኝ እጄን ትይዛለህ። በምክርህ ትመራኛለህ፤ በመጨረሻም በክብር ትቀበለኛለህ። በሰማይ ከአንተ ሌላ ማን አለኝ? በምድርስ አንተን ካገኘሁ ሌላ ምን እሻለሁ? አእምሮዬና ጒልበቴ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን እስከ ዘለዓለም ብርታቴና አለኝታዬ ነው። እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉ፤ አንተን የሚክዱህን ሁሉ ትደመስሳቸዋለህ። ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረቤ መልካም ነው፤ የአንተን ሥራ ሁሉ ለማብሠር እንድችል አንተን ጌታ አምላኬን መጠጊያዬ አድርጌአለሁ።
መዝሙር 73:15-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እንደዚህ እናገራለሁ” ብል ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር። አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ። ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ። በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ፥ በድንጋጤ ጠፉ። ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ መልካቸውን ትንቃለህ። ልቤ ነድዶአልና፥ ኩላሊቴም ቀልጦአልና፥ እኔ የተናቅሁ ነኝ አላወቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ። እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። በአንተ ምክር መራኸኝ፥ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ። በሰማይ ከአንተ ሌላ ማን አለኝ? በምድርስ ከአንተ ጋር ሆኜ ሌላ ምን እሻለሁ? ልቤና ሥጋዬ አለቀ፥ እግዚአብሔር ግን ዘለዓለም የልቤ ኃይልና እድል ፈንታዬ ነው። እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፥ በማመንዘር ከአንተ የሚርቁትን ሁሉ አጠፋኻቸው። ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፥ መጠለያዬም ጌታ ነው ሥራህን ሁሉ እናገር ዘንድ።